ቢሮው ከ22 የአሰሪና ሰራተኛ አደረጃጀቶች ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ

618

አዲስ አበባ፣  ጥር 16/2014(ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ፣ ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ከ22 የአሰሪና ሰራተኛ አደረጃጀቶች ጋር የስራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ፡፡

የመግባቢያ ሰነዱ በዋናነት በአሰሪና ሰራተኞች መካከል ጤናማ የስራ ግንኙነትን በመፍጠር የኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያለመ ነው፡፡

የስምምነት ሰነዱን የተፈራረሙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የስራ፣ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ፣የአሰሪ እና ሰራተኛ ማህበራት ተወካዮች እና የመንግስት አስፈጻሚ ተቋማት ናቸው።

ምክትል ከንቲባው አቶ ጃንጥራር አባይ የመግባቢያ ሰነዱ በአሰሪና ሰራተኞች መካከል የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስምምነቱ የቁጥጥር ስርዓት ለመዘርጋት፣የማህበራዊ ምክክር ስርዓት ለማጎልበት እንዲሁም አሰሪና ሰራተኞች ተመካክረውና ተግባብተው ለኢንዱስትሪ እድገት እንዲሰሩ በማስቻል ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም የማህበራዊ ምክክር ስርዓት ተግባራዊ እንዲሆን በማድረግ በአሰሪና ሰራተኞች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በአጠረ ጊዜ ለመፍታት እንደሚያግዝም አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበር ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን  ፎሎ፤ ሰነዱ የአሰሪና ሰራተኛውን የሚመለከቱ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ህጎችና ስምምነቶችን ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

ምቹና ጤናማ የስራ አካባቢ እንዲሁም ከአደጋ እና ከጤና ስጋት ነጻ የሆነ የስራ ሁኔታን እንደሚፈጥርም እንዲሁ፡፡

የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ታደለ ይመር በበኩላቸው ሰነዱ የአሰሪውንና ሰራተኛውን ጥቅም በማስጠበቅ  ምቹ የስራ ከባቢና ሰላምን ለማስፈን የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ኢንዱስትሪዎች በአገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ የድርሻቸውን ሚና እንዲወጡ እንደሚያግዝም ጠቅሰዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከ2 ሚሊየን በላይ ሰራተኞች በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ተሰማርተው እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡