በጦርነቱ የተጎዱ ንጹሃን ዜጎችን ማቋቋም፣ መደገፍና የወደመ ንብረታቸውን መተካት ከሁሉም ዜጎች ይጠበቃል

74

አዲስ አበባ፣  ጥር 16/2014(ኢዜአ) በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱ ንጹሃን ዜጎችን ማቋቋም፣ መደገፍና የወደመባቸውን ንብረት መተካት ከሁሉም ዜጎች እንደሚጠበቅ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ።

በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተዘጋጀው "አንድ ቤተሰብ ለአንድ ዳያስፖራ" ንቅናቄ መርሃ ግብር ትናንት ምሽት በይፋ ተጀምሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የታደሙት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴም አራት ሕጻናትን ባሉበት ቦታ እየደገፉ ለማሳደግ ቃል ገብተዋል።

ፕሬዚዳንቷ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር "አውዳሚነት ፈጽሞ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ አይደለም" ብለዋል።

በአገሪቷ መንግስታት ሲቀያየሩ በፖለቲካ ጉዳዮች አለመግባባቶች እንደሚፈጠሩ አስታውሰው በዚህ ደረጃ የሕዝብ መገልገያ መሰረተ ልማቶችን በማውደም በዜጎች ላይ ጉዳትና ውድመት አለመድረሱን ተናግረዋል።

በአሸባሪው ቡድን የተፈጸመው ተግባር የሚያሳየው የቡድኑ የፖለቲካ ፍላጎት በራሱ በውል የማይታወቅ መሆኑን ነው ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ የግፍ በትሩ በንጹሃን ዜጎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ችግሩን ይበልጥ አክብዶታል ነው ያሉት።

"የጦርነት ማብቃት የጥይት ድምጽ መቆም ብቻ አይደለም" ያሉት ፕሬዚዳንቷ በጦርነቱ የወደሙ መሰረተ ልማቶችና የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል።

በዚህ ረገድ ዳያስፖራው በመርሃ ግብሩ ለመሳተፍ ያሳየው ቀናኢነት የሚበረታታና ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባ ነው ብለዋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬም ጦርነት በጎ ጎን ባይኖረውም በአሸባሪው ህወሓት ወረራ የሕዝብ አንድነት፣ መደጋገፍና ለአንድ ዓላማ መቆም ጎልቶ ታይቷል ብለዋል።

ይህ መተባበር የተቀዛቀዘው ፓን አፍሪካኒዝም የተቀሰቀሰበትና ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ጉዳይ እንደማይደራደሩ ዓለም የተገነዘበበትም መሆኑም ጠቅሰዋል።

አሸባሪው ቡድን በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች የፈጸማቸው ሠብዓዊ ጥፋቶችና ውድመቶች ከሰብአዊነት ያፈነገጠ መሆኑን ዳያስፖራዎቹ በጉብኝታቸው እንዳረጋገጡ እሙን ነው ብለዋል።

የ"አንድ ቤተሰብ ለአንድ ዳያስፖራ" መርሃ ግብር ቤታቸው የወደመባቸውን ቤተሰቦች፣ ያለ ወላጅ የቀሩ ህፃናት፣ ጧሪ ቀባሪ ያጡ አረጋዊያን፣ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች መልሶ ማቋቋምና መደገፍ ላይ እንደሚያተኩርም አብራርተዋል።

መርሃ ግብሩ አንድ ዳያስፖራ የመረጠውን ቤተሰብ የሚያቋቁምበት እንደሆነም አክለዋል።

ሚኒስትሯ ጥሪውን ተቀብለው ቤተሰብ ለመደገፍ ፍቃደኛ የሆኑ የዳያስፖራ አባላት የበጎ ተግባሩን መጀመር እንደሚችሉም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሃመድ እንድሪስ አገራዊ ጥሪውን ተቀብለው ወደ አገራቸው የመጡ ዳያስፖራዎች የመጡበትን ዓላማ እያሳኩ ነው ብለዋል።

በተለይም የተጎዱ አካባቢዎችና ዜጎችን በመጎብኘትና በመደገፍ እንዲሁም ለድጋፍ በተዘጋጁ የተለያዩ አማራጮች መሳተፋቸው ተገልጿል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ዲያስፖራው ከ1 ነጥብ 28 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉንም አስታውቀዋል።

የተጎዱ ቤተሰቦችን በመደገፍና በማቋቋም በአይነቱ የመጀመሪያ በሆነው መርሃ ግብር በመሳተፍ ያሳያችሁት መነሳሳት ተምሳሌት ያደርጋችኋል ነው ያሉት።

በዚህና መሰል ስራዎች ኤጀንሲው የሚያደርገውን ድጋፍና እገዛ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዶክተር መሃመድ አረጋግጠዋል።

በመርሃ ግብሩ የተሳተፉ ዳያስፖራዎች የሚያግዟቸው ቤተሰቦች ያሉበት አካባቢ፣ የቤተሰብ ብዛትና የሚያስፈልጓቸውን ዝርዝር ነገሮች በሚገልጽ ፎርም ላይ ሃሳባቸውን በማስፈር ለማቋቋም ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

አሸባሪው ቡድን በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች ህጻናት የተጋፈጡትን አስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ የሚያሳይ ስዕል ለጨረታ ቀርቦ በ2 ሚሊዮን ብር የተሸጠ ሲሆን ገንዘቡ ለድጋፍ መርሃ ግብሩ ማስፈጸሚያ ውሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም