በሀገሪቱ የመጣው ለውጥ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ መነቃቃትን ፈጥሯል - የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር

66
ነሐሴ 24/2010 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ እየታየ ያለው ለውጥ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ መነቃቃት እየፈጠረ መሆኑን የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የሚኒስቴሩ የህዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ ለኢዜአ እንዳሉት ለውጡን ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መግባት ጀምረዋል፡፡ ዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙኃን የሀገሪቱን መልካም ገጽታ የሚገነቡ ዘገባዎችን በስፋት ማስተጋባት መጀመራቸውም በጎብኚዎች ፍሰት ላይ አወንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡ ሚኒስቴሩ ዘርፉን በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ ለመምራት ከክልል መዋቅሮች ጋር መፈራረሙንም ነው አቶ ገዛኸኝ የተናገሩት፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅትን በአዲስ መልኩ ለማደራጀት የሚያስችለው ጥናት እየተጠናቀቀ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ይህም ለዘርፉ መነቃቃት የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል፡፡ አቶ ገዛኸኝ እንዳሉት በታቀደው ልክ ባይሆንም ያለፈው በጀት ዓመት የጎብኝዎች ፍሰትና የተገኘው ገቢ የተሻለ ነበር፡፡ በተለይ በበጀት ዓመቱ የመጨረሻ ወራት መታየት የጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ የተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት ለዘርፉ ብሩህ ተሰፋ መፈንጠቁንም ነው ያብራሩት፡፡ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው በ2010 በጀት ዓመት ወደ ሀገሪቱ ከመጡ ጎብኝዎች 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ አፈጻጸሙ ከእቅዱ ጋር ሲነጻጸር 75 በመቶ ሲሆን እቅዱ ሙሉ ለሙሉ ላለመሳካቱ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመትም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ጎብኝዎችን በማስተናገድ ከአምስት ቢሊዮን የሚበልጥ የአሜሪካ ዶላር  ለማግኘት እቅድ ተይዟል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም