ዩኒቨርስቲው ለማስፋፊያ ለወሰደብን የእርሻ መሬት ካሳ ባለመክፈሉ ለችግር ተዳርገናል---አርሶ አደሮች

74

ሚዛን፣ ጥር 16/2014 (ኢዜአ) የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ለማስፋፊያ ለወሰደብን የእርሻ መሬት ካሳ ባለመክፈሉ ለችግሮች ተዳርገናል ሲሉ አርሶ አደሮች ቅሬታቸውንም ገለጹ።

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የእርሻ መሬታቸውን ለማስፋፊያ ከወሰደ ከሶስት ዓመት ወዲህ በይዞታቸው ማልማት ሆነ መጠቀም ባለመቻላቸው ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን አርሶ አደሮቹ ቅሬታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል  ።

አርሶ አደሮቹ ከሦስት ዓመት በፊት የእርሻ ቦታቸውን ከዩኒቨርስቲው ጋር ባደረጉት ስምምነት መልቀቃቸውን ገልጸው ስምምነቱ ካለመፈጸሙ በተጨማሪ በማሳቸው ላይ የነበራቸው ቋሚ ተክል እንኳ መጠቀም እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

ከቅሬታ አቅራቢዎች መካከል አርሶ አደር መንግስቱ ደበበ እንዳሉት ዩኒቨርስቲው ለማስፋፊያ ግንባታ በሚል የእርሻ መሬታቸውን ከተወሰደ በኋላ ካሳ ሳይከፍላቸው ቆይቷል።

ካሳ ሳይከፈላቸውና መሬታቸውን አልምተው መጠቀም ሳይችሉ ሦስት ዓመት እንዳለፋቸው ተናግረዋል።

ቀድሞ ያለሙትን የቡናና ሙዝ ምርት እንኳን ሳይጠቀሙ መቅረታቸውን አውስተዋል።

"ከካሳ  ወይም ከይዞታችን  ከአንዱ ሳንሆን ለችግር ስንዳረግ ዩኒቨርስቲው ለቅሬታችን እልባት ሊሰጥ አልቻለም" ያሉት አርሶ አደሩ "ለቀለባችንና የልጆቻችን ማስተማሪያ የሆነው ማሳ ጾሙን እያደረ ችግር ውስጥ ወድቀናል" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

ሌላው አርሶ አደር አለሙ ኪሊ በበኩላቸው "ለዩኒቨርሲቲው ማስፋፊያ ግንባታ ለለቀቅነው መሬት ዛሬ ነገ እየተባለ ካሳ ሳይከፈለን ሦስት ዓመት ተኩል በመቆየታችን ተቸግረናል"  ብለዋል።

አርሶ አደሩ በማሳቸው ጎደሬ፣ ሙዝና ቡና አልምተው ይተዳደሩ እንደነበር አስታውሰው ለይዞታቸው ካሳ ሳይከፈላቸው ወይም ሌላ አማራጭ ሳይታሰብላቸው እንዲሁ አመታት ለመቆየት መገደዳቸው ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል።

"ለዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች በተደጋጋሚ ቅሬታ ብናቀርብም ከጊዜ ቀጠሮ ውጭ ከሶስት አመታት በላይ የተሰጠን መፍትሔ የለም" ያሉት ደግሞ  ወይዘሮ ወገኔ ለገሠ ናቸው ።

ወይዘሮ ወገኔ ልጆቻቸውን ማስተማር እንዳልቻሉና ለችግር እየተዳረጉ መሆናቸውን ገልጸው "ዩኒቨርሲቲው በብዙ ማሳመኛ አሳምኖን ቦታውን ከተረከበ በኋላ ሌላው ቀርቶ የተገመተውን ካሳ እንኳ ሊከፍል አልቻለም" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል ።

"አርሶ አደሮቹ ዩኒቨርሲቲውም ሆነ የሚመለከተው የመንግስት አካል ቅሬታችንን ተመልክቶ በቶሎ መፍትሔ ሊሰጠን ይገባል" ሲሉ ጠይቀዋል።

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አህመድ ሙስጠፋ አርሶ አደሩቹ ላቀረቡት ቅሬታ በሰጡት ምላሽ ዩኒቨርሲቲው ለማስፋፊያ ግንባታ በአማን ከተማ ከኮመታ ቀበሌ ነዋሪዎች 65 ሄክታር የእርሻ መሬት በስምምነት መውሰዱን ተናግረዋል ።

በይዞታው ላይ ለነበሩ የተለያዩ ተክሎች ካሳ ከፍሎ ነዋሪዎችን ለማስነሳት ስምምነት እንዳለ አውስተዋል።

አርሶ አደሮቹ በማሳቸው ላይ ባለ ቋሚ ተክል ለመጠቀምም ሆነ ለማልማት እንዳልቻሉ በተደጋጋሚ ቅሬታ ማቅረባቸው ተገቢነት ያለው መሆኑን ዶክተር አህመድ ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው 1 ሺህ 37 ከሚሆኑ ከአርሶ አደሮች በስምምነት ቦታውን ከተረከበ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ እንደሆነው ጠቁመው "ይሁንና የዩኒቨርስቲው ሥራ አመራር በማስፋፊያ ግንባታው ላይ በመግባባት ከተቀበለው አንድ ዓመት ጊዜ አልሞላውም" ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ለማስፋፊያ በወሰደው መሬት ላይ ለሚገኝ ንብረትና ለይዞታ ካሳ ክፍያ ከ450 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት እንደሚጠይቅ ገልጸው ለነዋሪዎች ቅሬታ በቂ ምላሽ ለመስጠት የበጀት እጥረት ማነቆ ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ በጉዳዩ ላይ ከሚመለከተው አካልና ከዩኒቨርሲቲው ቦርድ ጋር በድጋሚ በመመርመር መፍትሄ ለመስጠት ቁርጠኝነት እንዳለ አመላክተው ዩኒቨርሲቲው ከይዞታቸው ለተነሱ አርሶ አደሮች ጊዜያዊ ችግር ማቃለያ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን ተናግረዋል ።

የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪና የዩኒቨርስቲው ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ቀበሌ መንገሻ "ለተፈጠረው ችግር ከሌሎች ጉዳዮች አስቀድሞ መፍትሄ ለመስጠት አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን" ብለዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ነዋሪዎቹ መስተጓጎላቸውን የጠቆሙት አቶ ቀበሌ አርሶ አደሮቹ ላነሱት ቅሬታ ባጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ እንዲያገኙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም