ቻይና የአለም ኦሎምፒክ ጨዋታን በተሻለ መልኩ እንደምታዘጋጀው ተስፋ አለኝ- ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ

679

ጥር 16 ቀን 2014 (ኢዜአ)የብዙ ሪከርዶች ባለቤት የሆነው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ከዥንዋ ጋር በነበረው ቆይታ ቻይና ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መልኩ የ2022 የክረምት ኦሎምፒክን እንደምታዘጋጅ ያለውን ተስፋ ገለፀ፡፡

አትሌት ኃይሌ ቻይና በ2022 በቤጂንግ ክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታዎች “አረንጓዴ እና ንፁህ” የኦሊምፒክ ውድድርን ለአለም እንደምታሳይ ተስፋ አለኝ ብሏል።

ቻይናውያን ጨዋታውን በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ እንደሚያቀርቡት የገለጸው አትሌት ኃይሌ፤ጨዋታው አስደናቂ እና ማራኪ ክስተቶች እንደሚኖሩትም ተናግሯል፡፡

የቻይና መንግስት የ2022 የቤጂንግ የክረምት ኦሊምፒክ ጨዋታዎችን ስኬታማ ለማድረግ የሚያደርገው ጥረት ሃገሪቱ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰጠችውን ክብርና ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደሆነም ገልጿል፡፡

በ2008 የተካሄደው የኦሊምፒክ ጨዋታ አስደናቂ እንደነበር ያስታወሰው አትሌት ኃይሌ፤የሚመጣው የቤጂንግ ክረምት ኦሊምፒክም የጨዋታ ደረጃዎችን ከፍ በማድረግ በቀጣይ ለሚካሄዱ ጨዋታዎች ጥሩ ምሳሌ ይሆናል ብሏል።

አትሌት ኃይሌ መጪው የክረምት ኦሊምፒክ አፍሪካውያን ትልልቅ ኩነቶችን እንዴት ማዘጋጀት እንደሚቻል ትምህርት የሚያገኙበት አጋጣሚ እንደሚሆን ገልጿል።

የአለም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የአለምን ህዝብ በአንድነትና በአንድ አላማ እንዲቆም ለማድረግ አረንጓዴ የኦሊምፒክ ጨዋታ ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝቧል።