መንግስት ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል

94

ጥር 16/2014/ኢዜአ/ መንግስት ድርቅ በተከሰተባቸው የአርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ገለፁ።

በተያዘው ዓመት በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የአገሪቷ አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች የተከሰተው የድርቅ አደጋ 'ላሊና' የሚሰኝ የአየር ንብረት መዛባት ያስከተለው ነው።

ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ለኢዜአ እንደገለጹት በሶማሌ ክልል 9 ዞኖች፣ በኦሮሚያ ክልል የቦረናና የምስራቅ ጉጂ እንዲሁም የሐረርጌና የባሌ ቆላማ አካባቢዎች በድርቁ ተጠቅተዋል።

በደቡበ ክልልም የኮንሶ፣ ጋሞ፣ ጎፋና ወላይታ ቆላማ አካባቢዎች እንዲሁም የደቡብ ኦሞ ዞን በድርቁ ተጠቅተዋል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ የድርቅ አደጋው 6 ሚሊዮን በሚጠጉ ዜጎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራው የብሔራዊ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ የድርቅ አደጋውን መቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ምክክር ማድረጉን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ድርቁ በተከሰተባቸው ክልሎችም በፌዴራል ደረጃ ያለውን አደረጃጀት የተከተለ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በክልሎች የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከላት በማቋቋም ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መገባቱንና በመንግስትና በዓለም ምግብ ፕሮግራም በኩል ድጋፎች እየቀረቡ መሆኑንም አክለዋል።

ከምግብ ነክ ድጋፍ ባሻገር የውሃ አቅርቦትና ተንቀሳቃሽ የሰዎችና የእንስሳት ጤና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንና እነዚህን ድጋፎች አጠናክሮ መቀጠል እንደሚጠይቅም ተናግረዋል።

የክልል የአደጋ ስጋት የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከላቱን በማጠናከር 24 ሠዓት እንዲሰሩ በማድረግ የድርቅ አደጋውን የመቀልበስ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም