የባህር ዳር ከተማ በህልውና ዘመቻው ለተሰዉ ቤተሰቦች የመኖሪያ ቤትና የመስሪያ ሱቅ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ወስኗል - ኢዜአ አማርኛ
የባህር ዳር ከተማ በህልውና ዘመቻው ለተሰዉ ቤተሰቦች የመኖሪያ ቤትና የመስሪያ ሱቅ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ወስኗል

ባህር ዳር፣ ጥር 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የአገራቸውንና የህዝባቸውን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ሲሉ በህልውና ዘመቻው በግንባር ተሰልፈው ለተሰዉ ጀግኖች ቤተሰቦች የመኖሪያ ቤትና የመስሪያ ሱቅ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው መወሰኑን አስታወቀ።
የአስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ በትግሉ ተስፋሁን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አገርን ለማፍረስ አቅዶ የተነሳውን የህወሓት አሸባሪ ቡድን ለመደምሰስ በርካታ የጸጥታ አካላት ከባህር ዳር ከተማ ወደ ግንባር ዘምተዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ኮሚቴ ለህዝባቸውና ለአገራቸው ሲሉ አሸባሪውን ቡድን ሲፋለሙ መስዋትነት ለከፈሉ ጀግኖች የቀበሌ የመኖሪያ ቤት ቅድሚያ እንዲሰጣቸው መወሰኑን ገልፀዋል።
በተጨማሪም በተለምዶ "ጋጃ መስክ" ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከተመሰረተው የገበያ ቦታ የመስሪያ ሱቅ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው መወሰኑን ተናግረዋል።
የመኖሪያ ቤት የሚያገኙት ከዚህ በፊት መኖሪያ ቤት ለሌላቸው የጀግና ቤተሰቦች መሆኑን ጠቁመው፤ ለንግድ ስራ የሚሆን የገበያ ቦታ ወይም ሱቅ ለሁሉም የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል።
"ከተማ አስተዳደሩ በጀግንነት ለተሰው ቤተሰቦች የሚያደርገው ድጋፍ ጀግኖቹ የከፈሉትን ዋጋ ይተካል በሚል ሳይሆን ከቤተሰቦቻቸው ጎን አለን ለማለት ነው'' ሲሉም ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ከዚህ በተጨማሪ ለጀግኖች ቤተሰቦች የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ በትግሉ፤ "ህብረተሰቡን በማስተባበር ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼