በአሸባሪው ህወሀት የወደሙ ኢንዱስትሪዎች መልሰው እንዲቋቋሙ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል- አቶ መላኩ አለበል

162

ደሴ (ኢዜአ) ጥር 15/2014–በአሸባሪው የህወሓት ቡድን የወደሙ ኢንዱስትሪዎች መልሰው እንዲቋቋሙና ወደ ሥራ እንዲገቡ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል አስታወቁ።

በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን መልሶ በማቋቋም ወደስራ ለማስገባትና ኢቨስትመንትን ለማነቃቃት ያለመ የምክክር መድረክ ዛሬ በደሴ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ንጹሀንን በግፍ ከመግደል ባለፈ ንብረት ዘርፏል፣ ያልቻለውንም አውድሟል።

ቡድኑ በክልሎቹ በፈፀመው ወረራም በ87 ከፍተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ላይ ውድመትና ዘረፋ መፈጸሙን ተናግረዋል።

“በየደረሰበት ብዙ ፋብሪካዎችን ሙሉ በሙሉ ነቃቅሎ የወሰደ ሲሆን ያለወሰዳቸውንም በቀላል ጠግኖ ለአገልግሎት እንዳይበቁ በማድረግ አሳዛኝና በታሪክ የማይረሳ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ አልፏል” ብለዋል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት የደረሰው ውድመት በአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ላይ ጫና ከማሳደር ባለፈ በከተሞች ገቢ እንዲቀንስ፣ ሥራ አጥነት እንዲበራከትና የብዙዎች ኑሮ እንዲናጋ አድርጓል።

“ኢንዱስትሪዎቹ ተጠግነው መልሰው ወደስራ እንዲገቡ መንግስት የሚችለውን ድጋፍ በማድረግ በዘርፉ ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ ይሰራል” ሲሉ አስታውቀዋል።

“በቅንጅት በመስራት በቀላሉ ተጠግነው ወደ ሥራ መግባት የሚችሉትን ኢንዱስትሪዎች ሥራ እያስጀመርን ነው” ያሉት ሚኒስትሩ፣ በሽብር ቡድኑ ጥፋት ተቆጭተው በራሳቸው ወደ ስራ የገቡ ባለሃብቶች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ በተለይ በከፍተኛና በመካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ላይ የደረሰው ውድመት የማጥናትና በቅድሚያ ድጋፍ የሚፈልጉትን  የመለየት ሥራ እየተሰራ ነው።

በጥናቱ መሰረት ጥሬ እቃ ከውጭ በነጻ ለሚያስገቡት፣ የብድር እፎይታና ብድር ለሚፈልጉ እንዲሁም ለሌሎችም እንደየ ጥያቄያቸው ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በፌዴራል ደረጃ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደስራ ተገብቷል።

የወደሙ ኢንዱስትሪዎች ተቋቁመው ሥራ እንዲጀምሩና ለበርካታ ሥራ አጦች የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ መንግስት በሚችለው እገዛ እንደሚያደርግ የጠቆሙት ሚኒስትሩ ዳያስፖራው ባለሃብቱና ህብረተሰቡ በሚችሉት ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው እንዳሉት በሽብር ቡድኑ ጉዳት ከደረሰባቸው 541 ከፍተኛ፣ መካከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች መካከል በቀላሉ መስተካከል የሚችሉ 60 የኢንዱስትሪ ፋብሪካዎችን በከፊል ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉን ተናግረዋል።

“ለቀሪዎቹ አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎ ሥራቸውን እንዲጀምሩ በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል” ብለዋል።

ኃላፊው እንዳሉት ፋብሪካዎች በመውደማቸው ከ12 ሺህ በላይ ቋሚ ሠራተኞች ከሥራ ውጭ የሆኑ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ቀሪዎቹን ወደ ስራ ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው።

በተለይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን የምስራቅ አማራ ዞኖች በመደገፍ ኢንቨስትመንቱን ለማነቃቃት የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ነው ያስታወቁት።

በ400 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው የኮምቦልቻ ችፑድ ፋብሪካ በህወሓት የጥፋት ቡድን መዘረፉንና መውደሙን የገለጹት ደግሞ ፋብሪካውን ወክለው በመድረኩ ላይ የተገኙት አቶ ደጀን አለልኝ ናቸው።

በፋብሪካው ማምረቻ ማሽኖችን ጨምሮ ሌሎች ንብረቶች በመጎዳታቸው ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰበት ተናግረዋል።

ፋብሪካው ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ ለአገር የውጭ ምንዛሬ ገቢ ያስገኝ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ፋብሪካውን መልሶ ሥራ ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፍአለን ጨምሮ የፌደራልና የክልል አመራሮች፣ ባለሃብቶችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡