የጋምቤላ ክልል በአማራና አፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ያሰባስባል

199

ጋምቤላ፣ ጥር 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጋምቤላ ክልል ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ቢሮ የወጣት አደረጃጀቶችን በመጠቀም በአማራና በአፋር ክልሎች አሸባሪው ህወሃት ወረራ በፈጸመበት ወቅት ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማሰባሰብ መዘጋጀቱን አስታወቀ።

ቢሮው የድጋፍ የማሰባሰብ መርሃ ግብሩን ውጤታማ ለማድረግ ከወጣቶች አደረጃጀትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋምቤላ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ክርሚስ ሌሮ እንዳሉት፤ ድጋፉን ለማሰባሰብ የታቀደው ‘‘ወጣትነቴ ለሀገሬ’’ በሚል መሪ ሃሳብ በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ በሚካሄድ የድጋፍ የማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ነው።

የወጣቶች ፌዴሬሽን፣ የወጣቶች ፎረምና ሌሎች የወጣቶች አደረጃቶች በመርሃ ግብሩ ተሳትፎ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።

የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ ለአንድ ወር ያህል እንደሚቆይ ኃላፊዋ ጠቁመዋል።

በአፋርና በአማራ ክልሎች የደረሰው ግፍ በጋምቤላ ክልል ህዝብ እንደደረሰ የሚቆጠር መሆኑን ገልጸው፤ “ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ቢሮው ከወጣት አደረጃጀቶች ጋር በመሆን የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ይሰራል” ብለዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሯች ባየህ በበኩላቸው “የሽብር ቡድኑ የፈጠረውን ችግር ለመሻገር የመተባበርና የመደጋገፍ ባህል ተጠናከሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

እቅዱን ስኬታማ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ የወጣት አደረጃጀቶች ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳሰበዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙ የወጣት አደረጃጀት አመራሮች በሽብር ቡድኑ የተፈናቀሉ የአማራና የአፋር ክልል ወገኖችን ለመደገፍ የታለመውን እቅድ ለማሰካት እንደሚተጉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼