ከ57 ዓመት በኋላ እድሳት የተደረገለት የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ህንፃ ተመረቀ

160

ጥር 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከ57 ዓመት በኋላ ቅርስነቱንና ነባሩንገፅታ ሳይለቅ መሰረታዊ እድሳት የተደረገለት የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ህንፃ ተመረቀ፡፡

እድሜ ጠገቡ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ህንፃ ከ57 ዓመት በኋላ ቅርስነቱንና ነባሩን ገፅታ ሳይለቅ መሰረታዊ እድሳት ተደርጎለት ዛሬ ተመርቋል።

ያማረና ምቹ አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችል፣ የከተማዋን ገፅታና ዘመናዊነትን በተላበሰና ደረጃዋን በሚመጥን መልኩ መታደሱ ተገልጿል፡፡

ህንጻው በርካታ አዳዲስና ደረጃቸውን የጠበቁ አገልግሎቶችን በውስጡ ያካተተ ዘመናዊ እድሳት ተከናውኖለታል።

ከነዚህም ውስጥ የህፃናት መዋያ፣ ቤተ-መጽሀፍት ፣ የስልጠናና የምርምር ክፍሎች፣ ክሊኒክ፣ የቴአትር አዳራሽና ስብሰባ አዳራሾች ይገኙበታል።

በተጨማሪም የሰራተኞች እና የባለጉዳዮች መመገቢያ አዳራሽ ፣ የተለያዩ ቢሮዎችን ያቀፈ ሲሆን በቂ የመኪና ማቆሚያ ፣ አረንጓዴ ስፍራዎችንና የከተማ ግብርናን በውስጡ አካቷል።

ታሪክ እሴትና ዘመናዊነት የተላበሰው የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ህንፃ የተደረገለት መሰረታዊ እድሳት የከተማዋን ገፅታ በመቀየርና የተለወጠ አስተሳሰብ በማምጣት በኩል አይነተኛ ሚና ይጫወታል ተብሏል።

“ይህ ህንፃ የትውልዱ ታሪክ ሃብትም ቅርስም ገፀበረከትም ነው፣ በመሆኑም ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ለህዝብ ክፍት የሚደረግ በመሆኑ ኑ እና ቤታችሁን ጎብኙ” ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጽ ጥሪ አቅርበዋል።

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ሃላፊዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።