በክልሉ ውጤታማ ስፖርተኞችን ለማፍራት ይሰራል

268

አርባ ምንጭ ጥር 15/2014 (ኢዜአ)—በደቡብ ክልል በሁሉም የስፖርት አይነቶች ውጤታማ ስፖርተኞችን ለማፍራት የስፖርት ህዝባዊ መሰረትና አደረጃጀትን ለማጠናከር እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አስታወቁ።

የክልሉ የስፖርት ምክር ቤት 21ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ርስቱ ይርዳው እንዳሉት ስፖርት አንድነትን፣ መተባበርንና ፍቅርን በማጽናት የበለፀገ ማህበረሰብ ለመፍጠር ወሳኝ ነው።

“በክልሉ ባለፉት ዓመታት ስፖርትን ለማስፋፋት በተደረገው ጥረት የኢትዮጵያ ኩራት የሆኑ ስፖርተኞችን ማፍራት ተችሏል” ብለዋል።

“ይሁንና የተገኘው ውጤት ክልሉ ካለው አቅም አንፃር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም” ያሉት እቶ ርስቱ፣ ይህን ለማሻሻል የሁሉም እካላት ብርቱ ጥረት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

በተለይ በሕልውና ዘመቻው የታየውን የህዝብ ህብረትና አይበገሬነት በማፅናት በክልሉ በሁሉም የስፖርት እይነቶች ስመ ጥር ስፖርተኞችን በብዛት ለማፍራት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ የስፖርቱን ህዝባዊነት፣ አደረጃጀትና አመራር ለማጠናከርና ለማገዝ እበክሮ እንደሚሰራም ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።

በቀጣይም ወጣቶች እንዳላቸው ዝንባሌ በዕውቀትና በክህሎት ብቁ እንዲሆኑ ድጋፍ የሚሰጥበት ሁኔታ እንደሚመቻችም ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ አባላትና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በቀጣይ ስፖርት ለህብረ ብሔራዊ እንድነት ያለውን የላቀ ሚና ለማጎልበት እንዲንቀሳቀሱም አሳስበዋል።

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ብላቱ በበኩላቸው በክልሉ የስፖርት ዘርፍ ዘመናዊ እደረጃጀትን ተከትሎ ህዝባዊ መሰረት እንዲይዝ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ምክር ቤቱ ለዘርፉ መጠናከር የሚረዱ ደንቦችና መመሪያዎች እንዲወጡ ገንቢ ሚና መጫወቱን አውስተዋል።

በዚህ ዓመት ከተከናውኑ ዋና ዋና ሥራዎች መካከል የተለያዩ ደንብና መመሪያዎች ተዘጋጅተው ለምክር ቤቱ መቅረባቸውንም ጠቅሰዋል።

ኃላፊው እንዳሉት ምርጥ ተስጥኦ ያላቸውን በመለየት በተመረጡ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በ82 ጣቢያዎች ላይ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና መርሃ ግብር ተጀምሯል።

በስልጠናው ለታቀፉ 2ሺህ 50 ታዳጊ ወጣቶች በተወሰነ ደረጃ  የስፖርት ትጥቆች ለማሟላት ጥረት የተደረገ ሲሆን፤ ቀሪውን የማሟላት ስራም እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።