በድሬዳዋ የኩላሊት ዕጥበት ህክምናን በመንግሥት የጤና ተቋማት ለማስጀመር እየተሰራ ነው

ድሬዳዋ ጥር 15/2014 (ኢዜአ) ...በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ የመንግስት ጤና ተቋማት የኩላሊት ዕጥበት ህክምናን ተደራሽ ለማድረግ እየተደረገ ያለው ርብርብ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለጹ።

በድሬደዋ ከተማ ገቢው ለኩላሊት እጥበት /ዲያሊስስ / መሳሪያ መግዣ የሚውል "ለክብር እራቱ" በሚል መሪ ቃል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ትናንት ተካሂዷል፡፡

በመርሃ ግብሩ የተሳተፉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሩ ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት የመጡ ዳያስፖራዎች፣  የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና  ታዋቂ ግለሰቦች በተናጠል 10 ሺህ ብር አበርክተዋል፡፡

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ለኩላሊት እጥበት ህክምና መሳሪያ መግዣና አገልግሎቱን ለማስጀመር በተከፈተ የባንክ አካውንትና  "በጎ ፍንድ ሚ" የድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆች ያሰባሰቡትን ጨምሮ  ከ4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ተበርክቷል፡፡

ከዚህ ሌላ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ  ከተለያዩ አካላት ቃል የተገባ ሲሆን፤ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለጨረታ የቀረበውን የግርግዳ ሰዓት በ400 ሺህ ብር በማሸነፍ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በተጨማሪም ድሬዳዋ የሚገኘው ናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን አንድ የኩላሊት ማጠቢያ ማሽን ገዝቶ ለመስጠት ቃል ገብቷል፡፡

ሕክምናውን ፈጥኖ ለማስጀመር የሚያስፈልገውን ገንዘብ  ለማሰባሰብ ድጋፍ የማድረጉና ቃል የመግባቱ ሂደት እንደቀጠለ ነው፡፡

የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ ከድር ጁሃር በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን፣ ባለሃብቶች፣ የድሬዳዋ ተወላጆች የሀገር ዕድገትን ለማጠናከርና ማህበራዊ ችግሮችን ለማቃለል እያበረከቱ የሚገኘውን ተግባራት አበረታተዋል፡፡

የኩላሊት እጥበት ማሽን በመንግስት ጤና ተቋማት አገልግሎት እንዲጀምርና የመክፈል አቅም የሌላቸውን ወገኖችን ህይወት ለመታደግ የተጀመሩ በጎ ተግባራት በህመሙ የሚሰቃዩ ወገኖችን በመታደግ በኩል  ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡

አስተዳደሩም የኩላሊት እጥበት ማሽን በመግዛት አገልግሎቱ እንዲጀመር ጥረት እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡

ከውጭ የመጡ የኢትዮጵያዊያን ሙሁራን በእውቀትና በገንዘባቸው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲን በመደገፍ የሀገርን ከፍታ ለማረጋገጥ ቃል መግባታቸው የሚያኮራና ለሀገር የሚከፈልን ፍቅር የሚያመለክት ነው ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የዲያስፖራዎች ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አቤል አሸብር በበኩላቸው እስካሁን ከውጭና ከሀገር ውስጥ ከተሰበሰበው ገንዘብ በተጨማሪ ቃል የመግባቱ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

የኩላሊት ህሙማን ቁጥርና የበሽታውም ገዳይነት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው በዓመቱ መጨረሻ እያንዳንዳቸው በቀን ለ20 ህሙማን አገልግሎት በሚሰጡ ሰባት የጤና ተቋማት ሕክምናው ይሰጣል ብለዋል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት ግቡን ለማሳካት በቅንጅት እየተሰራ ነው።

በገቢ ማሰባሰቢያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ለኩላሊት እጥበት ሥራ መጀመር አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም