25 ሺህ ሰዎችን ያሳተፈው የዘንድሮው የቶታል ኢነርጂስ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ

209

ጥር 15/2014/ኢዜአ/ 21ኛው የቶታል ኢነርጂስ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መነሻውንና መድረሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ ዛሬ ተካሄዷል።

የዘንድሮው ውድድር ሕዳር 5 ቀን 2014 ዓ.ም ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ተራዝሞ ዛሬ ተካሄዷል።

በሴቶች የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር በግሏ የተወዳደረችው ያለምዘርፍ የኋላው አሸናፊ ሆናለች።

አትሌቷ በታላቁ ሩጫ ኢትዮጵያ ውድድር ስታሸንፍ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን፤ በ2012 ዓ.ም በተካሄደው 19ኛው ውድድር አሸናፊ ነበረች።

አትሌት ግርማዊት ገብረእግዚአብሔር ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ 2ኛ እንዲሁም አትሌት መልክናት ውዱ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

በወንዶች በ2012 ዓ.ም 19ኛው የታላቁ የኢትዮጵያ ሩጫ ውድድር 3ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቆ የነበረው የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ አትሌት ገመቹ ዲዳ የዘንድሮውን ውድድር ማሸነፍ ችሏል።

የመከላከያ ስፖርት ክለብ ተወዳዳሪው አትሌት ጌታነህ ሞላ ሁለተኛ፤ አትሌት ቦኪ ድሪባ ከ’ኢሊት ስፖርት ማኔጅመንት ኢንተርናሽናል’ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ለ21ኛ ጊዜ ዘንድሮ በተካሄደው ውድድር በሁለቱም ፆታ አንደኛ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ እያንዳንዳቸው 100 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነዋል።

በውድድሩ ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁ ለእያንዳንዳቸው 30 ሺህ ብር እና ሶስተኛ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ 12 ሺህ ብር ሽልማት አግኝተዋል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሁለቱም ጾታዎች ከ1 እስከ 10 ላጠናቀቁ አትሌቶች በአጠቃላይ የ270 ሺህ ብር ሽልማት አበርክቷል።

በ21ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር የውጭ አገራት ዜጎች፣ ዳያስፖራዎች እንዲሁም በርካታ አትሌቶችን ጨምሮ 25 ሺህ ሰዎች ተሳትፈዋል።

በ2013 ዓ.ም በተካሄደው 20ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በ2012 ዓ.ም ከነበረው የተሳታፊዎች ቁጥር 25 በመቶው (12 ሺህ 500 ሰዎች) ብቻ መሳተፋቸው የሚታወስ ነው።