ከሱዳን ጋር ተቀራርበን መስራት እንደሚገባን መግባባት ላይ ደርሰናል

71

ጥር 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከሱዳን ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ተቀራርበን መስራት እንደሚገባን መግባባት ላይ ደርሰናል ሲሉ የአገር መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ።

የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ጄኔራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ በኢትዮጵያ የነበራቸውን የሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት አጠናቀው ዛሬ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ዶክተር አብርሃም አሸኛኘት አድርገውላቸዋል።

የጄኔራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎን የኢትዮጵያ ቆይታን በተመለከተ ዶክተር አብርሃም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያና በሱዳን የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዷል።

“አብረንና ተቀራርበን መስራት እንደሚገባን ተግባብተናል” ሲሉም ገልጸዋል።

ትናንት አዲስ አበባ የገቡት ጄኔራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።

ጄኔራሉ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ከአገር መከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ እና ከኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም