ዓመታዊው የአገው ፈረሰኞች በዓልን በተለያዩ ክዋኔዎች ለማክበር ዝግጅት ተጠናቋል-ማህበሩ

152

እንጅባራ ጥር 15/2014-(ኢዜአ) -የአገው ፈረሰኞች በዓልን ለ82ኛ ጊዜ በተለያዩ ክዋኔዎች በድምቀት ለማክበር የዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን ማህበሩ አስታወቀ።

አማራ ክልል በድምቀት ከሚከበሩ ሕዝባዊ በዓላት አንዱ የአገው ፈረሰኞች በአል ነው።

የአገው ፈረሰኞች ማህበር ከእንጅባራ ዩኒቨርሲቲና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር ጥር 23 ቀን 2014 ዓ.ም በእንጅባራ ከተማ የሚከበረውን በዓል አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ጥላዬ አየነው እንዳሉት በዓሉ አባቶች በአድዋ ጦርነት የፈጸሙትን ገድል ለመዘከር በየዓመቱ በታላቅ ድምቀት ይከበራል።

በጣሊያን ወረራ ጊዜ ጀግኖች አባቶች በፈረስ ተዋግተው ሀገርን ነጻ ያወጡበትን ድል ለማሰብ ከ1933 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ በዓሉ በአገው ፈረሰኞች ማህበር እየተከበረ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘንድሮ በዓሉን ጥንታዊ ባህሉን በሚያጎላ አግባብ በፈረስ ጉግስና በሌሎች ክዋኔዎች በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

በዓሉ በአገር ቅርስነት እንደተመዘገበ ሁሉ የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብም የሚመለከታቸው አካላት ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

“የጀግኖች አባቶችን አደራ ለመወጣት ማህበሩ በህልውና ዘመቻው አባላቱን ከማዝመት ባለፈ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በመደገፍ የድርሻውን ተወጥቷል” ብለዋል።

በተጨማሪም ማህበሩ ከዞን እስከ ቀበሌ ባለው አደረጃጀት የተጣላ በማስታረቅና ፍትህና ሠላም እንዲሰፍን በማድረግ ማህበራዊ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጋርዳቸው ወርቁ በበኩላቸው “ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው ባሻገር በቱሪዝም ዘርፍ የራሱን አስተዋጾ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው የአገው ፈረሰኞች በዓልን በጥናትና ምርምር በማስደገፍ የበለጠ እንዲታወቅ በማድረግ በአገር ቅርስነት ደረጃ በ2013 ዓ.ም እንዲመዘገብ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም በዓሉ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ለማድረግ በሚከናወኑ ተግባራት እገዛ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

“ፈረስ ለአገው ህዝብ የደስታ፣ የሀዘንና ሌሎች ክዋኔዎች መገለጫ ሲሆን ማህበሩም የፍትህና የሠላም እንዲሁም የጀግንነት ተምሳሌት ነው” ያሉት ደግሞ የአዊ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንግዳ ዳኛው ናቸው።

በዓሉ እውቅና አግኝቶ እየተስፋፋ እንዲመጣ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

“በዓሉ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቦና የቱሪስት መስህብ ሆኖ ሀብት እንዲያመነጭ ለማድረግ ይሰራል” ሲሉ አመላክተዋል።

የአገው ፈረሰኞች በዓል በየዓመቱ ጥር 23 የአገውን ባህል አጉልቶ በሚያሳይ አግባብ በፈረስ ጉግስ፣ በፓናል ውይይትና በሌሎች ክዋኔዎች በድምቀት የሚከበር ነው።

የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ የአገው ፈረሰኞች በዓልን እንደ አንድ የቱሪዝም መዳረሻ በማድረግ በተለይ ለዳያስፖራው ለማስተዋወቅ ከብሔረሰብ አስተዳደሩ ጋር በመሆን እየሠራ መሆኑ ተመላክቷል።

ሰላሳ አባላትን ይዞ በ1933 ዓ.ም የተመሰረተው የአገው ፈረሰኞች ማህበር በአሁኑ ወቅት የአባላቱ ቁጥር 59 ሺህ 323 መድረሱ ታውቋል።