በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ሁሉም ሊረባረብ ይገባል

59

ደሴ (ኢዜአ) ጥር 15/2014---በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ርብርብ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ጥሪ አቀረቡ።

አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት በምስራቅ አማራ ጉዳት የደረሰባቸው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን በማነቃቃት መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት ያለመ የምክክር መድረክ በደሴ ከተማ እየተካሄደ ነው።

ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በመድረኩ ላይ እንዳሉት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቆርጦ የተነሳው አሸባሪው ህወሓት በክልሉ ያልፈፀመው የጥፋት ተግባር የለም።

ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ የመንግስት ተቋማትንና የኢኮኖሚ ዋልታ የሆኑ ኢንዱስትሪዎችን በማውደምና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን በመፈጸም የክፋት ጥጉን በተግባር አሳይቷል።

የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋም መንግስት ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህን የመንግስት ጥረት በማገዝ በኩል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

"ተቋማትን መልሰን ስንገነባ ቀደም ሲል ከነበረው በተሻለ መልኩ ከመሆን ባለፈ የሥራ እድል መፍጠር በሚያስችል መልኩ መሆን ይኖርበታል" ሲሉም አክለዋል።

ከመልሶ ግንባታና ማቋቋም ጎን ለጎን ህብረተሰቡ አንድነቱን ጠብቆ በተደራጀ አግባብ የሽብር ቡድኑ ዳግም ለመውረር የሚያደርገውን ትንኮሳ እንዲመክት አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ እንዳሉት የሽብር ቡድኑ ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች በ541 ከፍተኛ፣ መካከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ላይ ጉዳት አድርሷል።

ፋብሪካዎችን ጠግኖ መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ ሲሆን፣ "እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴም መጠነኛ ጉዳት ከደረሰባቸው 60 የሚሆኑትን ወደ ስራ ማስገባት ተችሏል" ብለዋል።

መንግስት ቀሪዎችን ደረጃ በደረጃ ወደ ሥራ ለማስገባት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውንና የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩን አቶ መላኩ አለበልን ጨምሮ የፌደራልና የክልል አመራሮች፣ ባለሃብቶችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም