ለባለ ብዙ ትርጉሙ የመሪዎች ጉባኤ ስኬት ሁላችንም በህብረት

414

ጥር 28 እና 29 ቀን 2014 ዓ.ም 35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በህብረቱ ዋና መቀመጫ  አዲስ አበባ ይከናወናል፡፡ ከዋናው የመሪዎቹ ጉባኤ አስቀድሞም እንዲሁ ሁለት የተለያዩ ጉባኤዎች ይከናወናሉ፡፡ እነሱም 43ኛው የአፍሪካ ሕብረት የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ ስብስባ እና 40ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብስባዎች ናቸው፡፡ ሁለቱም ስብሰባዎች ለመሪዎቹ ጉባኤ የመወያያ አጀንዳ ለመምረጥ የሚደረጉ ስብሰባዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ ሰላም ናት፡፡ አንዳንድ ምዕራባውያን እና መገናኛ ብዙሃኖቻቸው እንደሚመኙት ሳይሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ወደ ሀገር ቤት ግቡ ጥሪን ተቀብለው የመጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆችን ተቀብላ እያስተናገደች መሆኗ፣ እነዚሁ ዜጎች እና ወዳጆች በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው ያለምንም የጸጥታ ስጋት የልማት እንቅስቃሴዎችንና በሽብር ቡድኑ የተፈጸሙ ጥፋቶችን እየጎበኙ መሆኑ፣ በርካታ ህዝብ የሚሳተፍባቸው የገና እና የጥምቀት በዓላት ያለአንዳች የጸጥታ ችግር ማክበር መቻሉን ለዚህ በማሳያነት ማቅረብ ይቻላል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ሀገራዊ ሁነቶች ያለምንም የጸጥታ ችግር መከናወናቸው እና እየተከናወኑም መሆናቸው የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የአፍሪካ ህብረት 35ኛው የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲከናወን ለመወሰናቸው በዋና ምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረት መጠናከር ያላት አቋም በመንግስት ስርዓት እና በመሪዎች መለዋወጥ ምክንያት የማይለዋወጥ፤ በጽኑ መሰረት ላይም የተመሰረተ  መሆኑን የአፍሪካ አባል ሀገራት ሲመሰክሩት የኖሩት ሀቅ ነው፡፡ ለዚህም ነው የህብረቱ ዋና መቀመጫ በአዲስ አበባ እንዲሆን ስምምነት ላይ የደረሱት፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ያላትን ጠንካራ አቋም፣ ለአፍሪካ ህብረት እውን መሆን ያበረከተችውን አስተዋጽኦ እና የአፍሪካ ጉዳዮች በአፍሪካውያን እንዲታዩ ያላትን ምክንያታዊ መርህ የተረዱ የዘመኑ የአፍሪካ መሪዎች 35ኛው የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ ይህንንም በአዎንታ ተቀብላ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገች ትገኛለች፡፡

በዓመት ሁለት ጊዜ መደረግ የነበረባቸው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤያት በዓለም አቀፉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት መሪዎቹ በአካል ተገናኝተው መወያየት አቋርጠው ነበር። በመሆኑም ተቋርጦ የነበረው ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ለማድረግ በመንግስት በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ የደህንነት ችግር ያለባት፤ አዲስ አበባም እንዲሁ በስጋት ውስጥ ያለች ከተማ በመሆኗ ዜጎቻቸው ለቀው እንዲወጡ ተደጋጋሚ የሀሰት መረጃ ሲያሰራጩ የነበሩ አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት ይህ ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዳይካሄድም ልዩ ልዩ ዘመቻዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ "አፍሪካዊ ወንድማማችነታችንን ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጠናከር በሚያስፈልገን በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች ተስማምተው የህብረቱ ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲደረግ በመወሰናቸው በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ" በማለት የምስጋና መልዕክት ያስተላለፉት፡፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረት እና ለአፍሪካ አንድነት መጠናከር እያበረከተች ያለችው ሚና ካላት የነጻነት ተምሳሌትነት አንጻር ከኢትዮጵያ የሚጠበቅ ልዩ ሀላፊነት መሆኑን መሀሪ ታደለ ማሩ የተባሉ ምሁር እኤአ በ2019 Ethiopia and the AU: Special responsibilities of a Host Nation በሚል ርዕስ በጻፉት ሀተታ ላይ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ መንግስታት ሲቀያየሩ ሳይቀየር እስካሁን የዘለቀው ለአፍሪካ አንድነት መጠናከር ያላት ጽኑ አቋም እንደሆነ የሚገልጹት ምሑሩ ለዚህም ብሔራዊ ጥቅሟን ለማረጋገጥ ጭምር ከአፍሪካ አህጉር አባል ሀገራት ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እና ስትራቴጂዋ በማካተት ተግባራዊ ስታደርግ መቆየቷን በማሳያነት ያቀርባሉ፡፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረት መጠናከር ካላት የረጅም ዘመን ተነሳሽነት፣ ሀገራዊ ታሪክ፣ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር፣ ከምትገኝበት የመሬት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ፣ ወታደራዊ ጥንካሬ፣ እየጨመረ ከሚመጣው ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷ፣ በአህጉሪቱም ሆነ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ፣ ሰላም እና ደህንነት ላይ ከምታበረክተው አስተዋጽኦ አንጻር በኢጋድ እና በአፍሪካ ህብረት ውስጥ ያላት ተጽዕኖ ፈጣሪነት እየጨመረ መምጣት የሚገባው ስለመሆኑም ይጠቀሳል፡፡

የአፍሪካዊያን አንድነት መጠናከር ጉዳይ ለኢትዮጵያ ቀዳሚ አጀንዳዋ ነው፡፡ ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጉባኤው በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ውሳኔ መተላለፉን ተከትሎ "ኢትዮጵያ - የአፍሪካዊነትን ጉዳይ እንደ መጀመሪያ አጀንዳዋ እንጂ እንደ ሁለተኛ አድርጋ ወስዳው አታውቅም" የሚል መልዕክት ያስተላለፉት።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረት መጠናከር ያላት ፍላጎት በሁኔታዎች ላይ የሚመረኮዝ አለመሆኑንም ለማጠየቅ “የአፍሪካን ጉዳይ በተመለከተ ጥንትም ሆነ ዛሬ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ናት” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አህመድ በአፍሪካዊነት ጉዳይ ላይ የማይዋዥቅ አቋም እንዳላት አበክረው መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገራትን ድጋፍ በምትሻበት በዚህ ወቅት መሪዎቹ ጉባኤው በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ውሳኔ ማሳለፋቸው "የኢትዮጵያን አቋም ቀደምት የአፍሪካ መሪዎች እንደተገነዘቡት ሁሉ፣ የዚህ ዘመን መሪዎችም ስለመገንዘባቸው ማሳያ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

የጉባኤው በአዲስ አበባ መካሄድ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው። ከነዚህ ጥቅሞች መካከልም ኢትዮጵያ ሰላም መሆኗን፣ ለአፍሪካ ጉዳዮች ያላትን የማይናወጥ ጽኑ አቋም፣ የኢትዮጵያን መልካም ሁኔታ ለአፍሪካውያን እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተግባር ለማሳየት እና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት መልካም አጋጣሚን ይዞ መምጣቱ ይጠቀሳሉ።

በኢትዮጵያ የጸጥታ ችግር አለ በሚል እና በሌሎችም የተሳሳቱ መረጃዎች ጉባኤው በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ ፍላጎት እንደነበር የገለጸው የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ በአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የተላለፈው ውሳኔ ለኢትዮጵያ ከተለመደው የጉባኤ ዝግጅት በላይ፤ ሰላም መሆኗን ከማሳየቱም በላይ የሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ረገድ ትርጉሙ ከፍተኛ መሆኑን በርካቶች እየገለጹት ይገኛሉ፡፡

ኢትዮጵያም በዚህ ወቅት ከአህጉሪቱ መሪዎች የተሰጣትን ሀላፊነት ለመወጣት አስቀድማ ብሔራዊ ኮሚቴ በማዋቀር ዝግጅት ማድረግ ጀምራለች፡፡ ይህን እና መሰል ጉባኤዎችን ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ ሀላፊነት ማግኘቷ አፍሪካውያን በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን እምነት የሚያሳይ ነው። ህብረቱ በአዲሱ ዓመት ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካትም የአፍሪካ አህጉርን የስርዓተ-ምግብ አቅም መገንባት፣ የሰው ሃብት ልማት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትን ማፋጠን የሚሉትን በመሪ ቃልነት ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

የተፈጥሮ ነዳጅ ሀብት ባለቤት ሳይኮንም አዳዲስ የልማት አማራጮችን በማመንጨትና ውጤታማነታቸውን በማረጋገጥ የልማትና የዕድገት ምሳሌ መሆን እንደሚቻል ለተቀሩት የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ ሆና መታየት ይጠበቅባታል የሚሉት መሀሪ ታደለ፤ ኢትዮጵያ እያለማች ያለችውን እንደ የመንገድ፣ የባቡር፣ የአየር ትራንስፖርት እና የኤሌክትሪክ ሀይል መሰረተ-ልማቶች ግንባታ እና ልማትን በጋራ ተጠቃሚነት መርህ እንዲመራ በማድረግ የአፍሪካ አህጉር ኢኮኖሚያዊ ትስስር ሞተር በመሆን የመሪነት ሚናዋን ማሳየት እንደሚጠበቅባት ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ በቀጣይ የአፍሪካ ህብረትን ለማጠናከር ያለባትን ልዩ ሀላፊነት በውጤታማነት ለመፈጸም እና የሚጠበቀውን ግብ ለማሳካት ህብረቱን የሚመለከት ልዩ እና ግልጽ ስትራቴጂ ነድፋ መስራት፤ የሚቀረጸውን ስትራቴጂ ወደ ተግባር በመተርጎም የአፍሪካ አህጉርን ለማጠናከር ግልጽ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን መንደፍ፣ አስፈላጊ ተቋማዊ አደረጃጀቶችን መፍጠር፣ የፋይናንስ ድጋፍ ማሰባሰብ፣ ወታደራዊ አቅምን ማሳደግ እና ማዘመን፣ የቴክኖሎጂና የምሁራን ሀብትን በአግባቡ መጠቀም ይጠበቅባታል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን እንግዳ ተቀባዩ ህዝብ የዚህ ዓይነቱን መልካም እድል በመጠቀም የተለመደ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን በማሳየት ለጉባኤው ስኬታማነትም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም