በወላይታ ዞን ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

107

ሶዶ፣ ጥር 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የወላይታ ዞን ገቢዎች ባለስልጣን ባለፉት በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።

የባለሥልጣኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መብራቱ ጳውሎስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው።

ዘንድሮ የተሻለ ገቢ ሊሰበሰብ የተቻለው ግብር ሳይከፍሉ ይሰሩ የነበሩ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊ መስመር ማስገባት በመቻሉ እንደሆነ ገልጸዋል።

ደረሰኝ የማይሰጡና ያለፈቃድ የሚሰሩ ነጋዴዎች መበራከት የገቢ አሰባሰብ ስራው ላይ ጫና ማሳደሩን የተናገሩት ኃላፊው፤ ደረሰኝ ሳይቆርጡ አገልግሎት ሲሰጡ የተገኙ 140 ነጋዴዎች በገንዘብ እንዲቀጡ፣ የስራ ቦታቸውን የማሸግና ፈቃድ የመሰረዝ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የግብር ከፋይ የሂሳብ መዝገብ በህጋዊ የሂሳብ ባለሙያ በማስጠናት 80 መዝገቦች ኦዲት ተደርገው 16 ሚሊዮን ብር መገኘቱንም ገልፀዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ግብር ከፋዮች ግብርን በወቅቱ በመክፈል ለሀገሪቱ ልማትና እድገት አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተለይ ሀገር አሁን ያለችበትን ፈታኝ ወቅት ማለፍ እንድትችል የሚሰበሰበው ግብር ያለው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

በወላይታ ዞን ከ30 ሺህ በላይ ህጋዊ የግብር ከፋዮች አሉ።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም