የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 360 ባለሙያዎች አስመረቀ

306

ሀዋሳ፣ ጥር 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በህክምናው ዘርፍ ያሰለጠናቸውን 360 ባለሙያዎች ዛሬ አስመረቀ።

ኮሌጁ ያስመረቃቸው በመደበኛው ህክምና ለ15ኛ ጊዜ፣ በስፔሻሊቲ ደግሞ ለስድስተኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ናቸው።

ከነዚህም 246 በመጀመሪያ ዲግሪ፣ 74 በሁለተኛ ዲግሪና 40 በህክምና ስፔሻሊቲ መመረቃቸውን በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ ኮሌጁ በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ከሚሰጠው ትምህርት ባሻገር ከ20 ሚሊዮን ለሚበልጥ ሕዝብ የህክምና አገልግሎት ይሰጣል።

በሀገሪቱ ባለፉት 30 ዓመታት በጤና አገልግሎት ዘርፍ መሻሻል ቢኖርም፤ አገልግሎቱን በብቃትና በጥራት እንዲሁም ፍትሃዊነቱን ጠብቆ ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ያሉትን ክፍተቶች ለመሙላት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው የተማረ የሰው ሃይል በማፍራት የሚጠበቅበትን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ዶክተር በሪሶ አመልክተዋል።

የዛሬዎቹ ተመራቂዎች ወደማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ ያገኙትን ዕውቀት በቅንነትና በታማኝነት ወደተግባር በመለወጥ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ አሳስበዋል።

ኮሌጁ የዛሬዎቹን ጨምሮ 4 ሺህ 600 በላይ የጤና ባለሙያዎች ማስመረቁን ከኮሌጁ የተገኘው መረጃ ያሳያል።