ጆይ ኦቲዝም ዳያስፖራው የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ልጆች እንዲደግፍ ጠየቀ

72

አዲስ አበባ፣  ጥር 14/2014(ኢዜአ) የኒያ ፋውንዴሽን ጆይ ኦቲዝም ማዕከል ዳያስፖራው በስሩ የሚገኙ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ልጆች እንዲደግፍ ጥሪ አቀረበ።

አገራዊ ጥሪውን ተቀብለው ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወደ አገር ቤት የመጡ የዳያስፖራ አባላት ዛሬ ማዕከሉን ጎብኝተዋል።

የኒያ ፋውንዴሽን የጆይ ኦቲዝም ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ እሌኒ ዳምጠው ከተመሰረተ 20 ዓመታት ስላስቆጠረው ማዕከል እንቅስቃሴ አብራርተዋል።

ማዕከሉም የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች በቤት ውስጥ ተደብቀው እንዳይቀሩ፤ ለማስተማርና ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ የተቋቋመ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

እነዚህን ልጆች ለመደገፍ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት ዲያስፖራዎች እንዲያግዙና አብረዋቸው እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከ26 ዓመት በላይ በካናዳ የኖሩት አቶ ደነቀው አስጨናቂ የማዕከሉን በጎ ተግባር መመልከታቸውን ገልፀው በሚችሉት አቅም ለማገዝና ሌሎች ሰዎችንም ለማስተባበር እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል። 

በኢጣሊያ ለ20 ዓመታት የኖሩት ወይዘሮ ገነት ጀማል በበኩላቸው የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ላይ ከተሰራ መለወጥ እንደሚችሉ አይቻለሁ ነው ያሉት።

ማዕከሉን የመደገፉ ስራ የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ የገለጹት በእንግሊዝ አገር ነዋሪ አቶ ዜናወርቅ ዘመድኩንም የበኩላቸውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም