በዓባይ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በመፍታት በጋራ ማልማትና መጠቀም ይገባል

234

እንጅባራ፤ ጥር 14/2014 (ኢዜአ) በዓባይ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በመፍታት በጋራ አልምቶ ከመጠቀም ውጭ ለብቻ እንደግ በሚል ፖለቲካ ስምምነት ማድረግም ሆነ የጋራ አቋም መያዝ እንደማይቻል የሠላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም ገለጹ።

ዩኒቨርሲቲዎች ከመማር ማስተማር ሥራቸው ጎን ለጎን የዓባይ ውሃ ልማቱን ከምንጩ ጀምረው በጥናትና ምርምር ለማገዝ ቁርጠኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በታላቁ ዓባይ ወንዝ መነሻ ሰከላ ወረዳ ዓመታዊ የግዮን በዓል ተከብሯል፤ “ስለዓባይ ያገባኛል የሚል ሁሉ” በሚል ፅሁፍ ቀርቦ በየምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች በስፋት ተወያይተውበታል።

ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም በምክክር መድረኩ እንዳሉት “በብዙ መልኩ ያላስተዋወቅነውና ያልተጠቀምነው ሀብት ቢኖር ዓባይ ነው” ብለዋል።

ሀብቱን በመጠቀም የኢኮኖሚ ምንጭ በማድረግ ዘላቂ እድገት ለማምጣት ኢትዮጵያውያን በቁጭት ማልማትና በብዙ መልኩ መጠቀም አለብን ሲሉም በአፅኖት ገልጸዋል።

”ዓባይ የብዙ ነገሮቻችን ምንጭ ነው”ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሀይማኖታዊ፣ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ገጽታ ያለው በሁሉም ዘርፍ የዓለም አጀንዳ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል።

ከኢትዮጵያ አልፎ የቀጠናውና የዓለም ፖለቲካዊ መነጋገሪያ በመሆን በውሃው አጠቃቀም ዙሪያ የተፋሰሱ ሀገሮችን በጎራ የከፈለ ችግር መሆኑን አመልክተዋል።

አገራቱ በአጠቃቀም ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ወደ ሠላም ለመምጣት በጋራ ማልማት እንጂ ለብቻ እንጠቀም በሚል ፖለቲካ ስምምነት ማድረግ እንዲሁም የጋራ አቋም መያዝ እንደማይቻል ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

የጋራ ሀብታችንን በጋራ የአካባቢ ጥበቃ፣ ከከተማ እና መሠረተ ልማት ዕቅዶች ጋር ተገናዝቦ መሠራት እንዳለበትም አብራርተዋል።

ውሃው ከምንጩ አንስቶ እንዲጎለብትና ተጠብቆ እንዲቆይ ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚ እንድንሆን መንግስት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ባለሀብቶች በተቀናጀ ዕቅድ መመራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጋርዳቸው ወርቁ በበኩላቸው ዓባይን አልምቶ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የዘርፉ ሙያተኞች ድጋፍ ያስፈልጋል።

”የወንዙን ምንጭ ዙሪያውን ባህር ዛፍ እየተከልን ምንጩ ሊጎለብትና አካባቢው ቱሪስት ሊስብ አይቻልም” ሲሉ ተናግረዋል።

ምንጩ በዘላቂነት እንዲጎለብት፣ ከመነሻው ጀምሮ እንዲለማ በጥናትና ምርምር ለማገዝ ዩኒቨርስቲው ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በበኩላቸው “ዓባይን ለማስተዋወቅ መጀመሪያ ‘ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ’ ከሚለው የዩኒቨርሲቲ ሞቶ ጀምሮ በቅርቡ ደግሞ የዓባይ ውሃ ጥናትና ምርምር ማዕከል አለን” ብለዋል።

የዓባይን ዋንዝ ይበልጥ ለማስተዋወቅና ከዘርፈ ብዙ ቱሩፋቶቹ ተጠቃሚ ለመሆን በማህበረሰብ አገልግሎት በማዕከል በኩል ጥናትና ምርምር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በምክክር መድረኩ ዓባይን ከመነሻው ጀምሮ ለማልማት እንዲቻል የሚያግዝ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ የተቀናጀ ኮሜቴ እንዲዋቀር ስምምነት ላይ ተደርሷል።

የግዮን በዓል የክልሉ ርዕሰ መስተዳደርና የፌደራል ከፍተኛ ሀላፊዎች በተገኙበት በዓባይ ምንጭ በሆነችው ሰከላ ወረዳ ለ4ኛ ጊዜ ትናንት ተከብሯል።