ቀይ መስቀል አገልግሎቱን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ቅርንጫፎቹን የማጠናከር ስራ እያካሄደ ነው

73

ጋምቤላ፤ ጥር 14/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አገልግሎቱን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ሁሉንም ቅርንጫፎቹ በተሻለ አመራርና የፋይናንስ አስተዳደር የማጠናከር ስራ እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ።

በማህበሩ የጋምቤላ ቅርንጫፍ 16ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሄዷል።

በጉባኤው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ዋና ፀሐፊ አቶ ጌታቸው ታዓ እንደገለጹት፤  ማህበሩ ጋምቤላ ጨምሮ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቹን አቅም በማጎልበት የሰብአዊ አገልግሎቱን ለማጠናከር በትኩረት እየሰራ ነው።

በተለይም በሰሜኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ሌሎች አጋር አካላትን በማስተባበር የተጠናከረ የሰብአዊ  ድጋፎችን እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሁን ላይም ማህበሩ አገልግሎቱን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ጋምቤላን ጨምሮ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ቅርንጫፎቹን በተሻለ አመራርና የፋይናንስ አስተዳደር የማጠናከር ስራ እያካሄደ መሆኑን አስታወቀዋል።

የጋምቤላ ቅርንጫፍ 16ኛ ጠቅላለ ጉባኤ ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በጉባኤው የማህበሩን ጥረት የሚደግፉ ጠንካራ የቦርድ አመራር እንደሚሰየሙ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በክልሉ የአምቡላንስ ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና፣ የበጎ ፍቃድና ሌሎችንም የሰብአዊ አገልግሎቶችን ለረጅም ዓመታት ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል።

ማህበሩ በተለይም ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት በክልሉ በሚጋጥሙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ቀዳሚ የሰብአዊ አገልግሎት ምላሽ በመስጠት ረገድ እያበረከተው ላለው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

በክልሉ ለሚያካሄዳቸው የሰብአዊ አገልግሎት ስራዎች መቀናት የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ዛሬ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ያለፉትን አራት ዓመታት የአፈጻጸም ሪፖርት አድምጦ በማጽደቅና ሰባት የስራ አመራር ቦርድ አባላትን በመምረጥ መረሃ ግብሩን አጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም