ተቋሙ አዲስ የሚያስገነባው ህንጻ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያስችለዋል

123

አዲስ አበባ ፣ ጥር 14/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዲስ የሚያስገነባው ህንጻ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችለው የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ተናገሩ፡፡

ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዲስ ለሚያስገነባው የባለ 36 ወለል የዋና መስሪያ ቤት ህንጻ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ባስቀመጡበት ወቅት ነው፡፡

በመርሃ-ግብሩ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ እና የተቋሙ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያን ጨምሮ ሌሎች የፌደራልና የአዲስ አበባ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች እና የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት የመንግስት የልማት ድርጅቶች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያላቸውን አበርክቶ ከፍ ለማድረግ የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጀመረውን የለውጥ ስራ በማጠናከር ከብልሹ አሰራር በጸዳ መልኩ ሃብቱን በውጤታማነት መጠቀም እንዳለበት አስገንዝበው፤ በተጨማሪ ለደንበኞቹ የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ተቋሙ አዲስ የሚያስገነባው ህንጻ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈና ተወዳዳሪ አገልግሎት ለመስጠት ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

ግንባታው ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆንና በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተጠናቆ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በበኩላቸው የአዲሱ ህንጻ ግንባታ መጀመር በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የደንበኞች አገልግሎት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ተቋሙ ያለበትን የቢሮ እጥረት በመቅረፍ ለኪራይ የሚወጣውን ሃብት እንደሚያስቀርም ነው የተናገሩት፡፡

ለተቋሙ ሰራተኞች ምቹ የስራ አካባቢን ለመፍጠር እንዲያስችልም እንዲሁ፡፡

የህንጻ ግንባታው ለመዲናዋ ነዋሪዎች ከሚፈጥረው የስራ እድል ባሻገር የቴክኖሎጂ ሽግግርን እንደሚያሳልጥ የተናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የስራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ናቸው፡፡

የአፍሪካና የዓለም የዲፕሎማሲ ከተማ ለሆነችው አዲስ አበባ ተጨማሪ ውበት እንደሚያላብሳትም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የህንጻ ግንባታው በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅና 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚደረግለትም በመርሃ-ግብሩ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም