የጣና ሐይቅን ከእምቦጭ አረም ስጋት የሚታደግ ሕዝባዊ ንቅናቄ በሚቀጥለው ሳምንት ይጀመራል

177

ጎንደር፤ ጥር 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጣና ሐይቅን ከእምቦጭ አረም ለመታደግ ከ120 ሺህ በላይ ሕዝብ የሚሳትፍበት ንቅናቄ በሚቀጥለው ሳምንት በማዕከላዊና ደቡብ ጎንደር ዞኖች እንደሚጀመር የጣና ሐይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የእምቦጭ አረም ማስወገድ ዘመቻ የ2013 ዓ.ም አፈፃጸምና የ2014 ዓ.ም ዕቅድ ትግበራ ዙሪያ በጎንደር ከተማ ዛሬ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አያሌው ወንዴ በመድረኩ እንደገለጹት በጣና ሐይቅና ዙሪያው የተከሰተው የእምቦጭ አረም አሁንም በስጋትነቱ እንደቀጠለ ነው።

አረሙን ለማስወገድ ባለፉት ዓመታት በሕዝብ ተሳትፎ ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም፤ ከአረሙ የመባዛት ባህሪ ጋር ተያይዞ አረሙ አሁንም ሐይቁን እንደወረረ መሆኑን አስረድተዋል።

አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል በከፈተው ጦርነት ሳቢያ አረሙን የማስወገድ ሥራው ተስተጓጉሎ እንደነበር ገልጸው፣ በሕልውና ዘመቻው የተገኘው ድል ንቅናቄውን ለማስጀመር እንደረዳም ገልጸዋል፡፡

በዚህም ሐይቁን በሚያዋስኑት በማዕከላዊና ደቡብ ጎንደር ዞኖች በሚገኙ 30 ቀበሌዎች በሕዝብ ተሳትፎ የሚወገድበት ንቅናቄ በመጪው ሳምንት በይፋ እንደሚጀመር አስታውቀዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት በመደበው 20 ሚሊዮን ብር ወጪ በሚካሄደው ዘመቻ ከሁለት ሺህ ሄክታር በላይ የሸፈነ አረም ለማስወገድ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

የክልሉ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሾመ አግማስ በበኩላቸው ሐይቁን ከአረሙ ለመታደግ ባለፉት ዓመታት በመንግሥትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተከናወኑ የአረም ማስወገድ ዘመቻ ስራዎች አበረታች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮው የበጋ ወቅትም የአረም ማስወገድ ዘመቻውን በሕዝብ ንቅናቄ የሚወገድበት የድርጊት መርሃ ግብር መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ከ400 ሺህ በላይ ሕዝብ በማሳተፍ በአረሙ የተወረረውን የሐይቁን 90 በመቶ ያህል ከአረሙ ማጽዳት እንደተቻለም ተናግረዋል፡፡

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት ለንቅናቄው ከሰው ጉልበት በተጨማሪ የአረም ማውጫ ማሽኖች ተዘጋጀታቸተዋል።

ሐይቁን በሚያዋስኑት በማዕከላዊና ደቡብ ጎንደር ዞኖች ሕዝብና በየደረጃው የሚገኙት አመራሮች ርብርብ እንዲደርጉም ጠይቀዋል፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የምስራቅ ደንቢያ ወረዳ የአካባቢ ጥበቃ አስተባባሪ አቶ መሰለ ተባባል በበኩላቸው በወረዳው ሐይቁን የወረረውን 820 ሄክታር የሸፈነ አረም ለማስወገድ ከ7 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚሰማሩ  ገልጸዋል፡፡