በአማራ ክልል የተፋሰስ ልማትን ለስራ እድል መፍጠሪያ ለማዋል እየተሰራ ነው

91

ደሴ ፤ ጥር 14/2014(ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሃት ጉዳት የደረሰባቸው ተፋሰሶችን በመጠገንና በማልማት ለስራ ዕድል መፍጠሪያነትና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት እንዲውሉ እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የምስራቅ አማራ የ2014 የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም የንቅናቄ መድረክ በወልድያ ከተማ ተካሂዷል ።

በመድረኩ የቢሮው ምክትል ኃላፊ ዶክተር አልማዝ ጊዜው እንደገለጹት፤ በአሸባሪው ህወሃት ሽብር ቡድን ከ4 ሺህ በላይ ተፋሰሶች፣ ከአንድ ሺህ 400 በላይ የተፋሰስ ጽህፈት ቤቶችና 343 ሞዴል የችግኝ ጣቢያዎች ላይ ጉዳት አድርሷል።

ከ49 ሺህ በላይ የእርሻ መሳሪያዎችና ከ306 ሚሊዮን ለተከላ የተዘጋጀ ችግኝ በማውደምና በመዝረፍ ጉዳት አድርሷል ነው ያሉት።

በቡድኑ ጉዳት የደረሰባቸውን ተፋሰሶችን በመጠገንና መልሶ በማልማት  ከ36 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠርና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተለይ በምስራቅ አማራ በሁለት ሺህ 697 ተፋሰሶች ለ14 ሺህ 843 ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በንብ ማነብ፣ የእንሰሳት መኖ፣ አትክልት፣ ፍራፍሬና እንስሳት ማድለብ  የስራ እድል ከሚፈጠርባቸው መስኮች መካከል እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ከአንድ ነጥብ 4 ሚሊዮን ህዝብ በላይ በማሳተፍ ከ129 ሺህ 700 ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ይከናወናልም ነው ያሉት።

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ሃላፊ አቶ አሊ ሰይድ በበኩላቸው፤በተያዘው የበጋ ወቅት አንድ ሺህ 300 በላይ ተፋሰሶች እንደሚለሙ ገልጸዋል።

በተፈጥሮ ሀብት ልማቱ ከ500 ሺህ ህዝብ በላይ በመሳተፍ ከ44 ሺህ ሄክታር መሬት ይለማል ብለዋል።

በሽብር ቡድኑ በርካታ ተፋሰሶችና ጽህፈት ቤቶች ቢወድሙም መልሰን በማልማት የስራ እድል መፍጠሪያ እንዲሆኑ በቅንጅት እየሰራን ነው ያሉት ደግሞ የሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ተገኘ አባተ ናቸው ።

በንቅናቄ መድረኩ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ ወይዘሮ አይናለም ንጉሴና  የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለውን ጨምሮ ሌሎችም አመራሮች ፣የግብርና ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም