መቱ ዩኒቨርሲቲ ከ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ግምት ያላቸው ኮምፒዩተሮች ለትምህርት ቤቶች ድጋፍ አደረገ

173

መቱ፣  ጥር 14/2014(ኢዜአ) መቱ ዩኒቨርሲቲ በኢሉባቦርና ቡኖ ደሌ ዞኖች ለሚገኙት ለ16 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ግምት ያላቸው ኮምፒዩተሮች ድጋፍ አደረገ።

ለትምህርት ቤቶች የተሰጠው ድጋፍ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የኢንጂነሪንግና ሒሳብ ትምህርት ማዕከላት ለማቋቋም እንደሚያግዙ ተመልክቷል።

ለትምህርት ቤቶቹ የተለገሱት ያለኔትወርክ የሚሰሩ 400 ኮምፒዩተሮች መሆኑንና በገጠር ትምህርት ቤቶች የዲጂታል ቤተ መጻህፍት አገልግሎት እንደሚሰጡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር እንደገና አበበ አስታውቀዋል።

ከአስፈላጊ ግብዓቶች ጋር የተለገሱት ኮምፒዩተሮች 10ሺህ ማጣቀሻ መጻህፍትን፣ የሁሉም ትምህርት ዓይነቶች የፕላዝማ ትምህርትን እንዲሁም 47 ሺህ ትምህርታዊ ጽሁፎች(አርቲክሎች) የተጫነባቸው መሆኑን  በድጋፉ ርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በትምህርት ቤቶቹ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከላት በማቋቋም የትምህርትን ጥራት እንዲረጋገጥና በዕውቀትና በክህሎት የሚወዳደር ትውልድን ለመፍጠር እገዛ እንደሚያደርጉ ነው ያመለከቱት።

የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ኢንጂነሪንግና ሒሳብ ትምህርት ማዕከላት የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ዕውቀትና ብቃት ያለው ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለማፍራት ወሳኝ መሆኑን ዶክተር እንደገና ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታትም ድጋፍ የሚያደርግላቸውን ትምህርት ቤቶች ቁጥር ወደ 60 እንደሚያሳድግ ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።

በኢሉባቦር ዞን የቡሩሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር መምህር ታደለ ፍሪሳ ፤ድጋፉ በትምህርት ቤቱ ዲጂታል ቤተ መጻህፍት በማቋቋም ተማሪዎቻቸው በሌሎች አካባቢዎች ከሚገኙ አቻዎቻቸው  ጋር ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚደግፍ ተናግረዋል።

 በድጋፉ በትምህርት ቤቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ኢንጂነሪንግና ሒሳብ ትምህርት ማዕከል በማቋቋም ተማሪዎቻቸውን ለከፍተኛ ትምህርት ለማዘጋጀት አስተዋፅኦ ያደርጋል ያሉት ደግሞ በቡኖ በደሌ ዞን የደንቢ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አበራ ሚጀና  ናቸው።

በተለይም በማዕከሉ የሚሰጠው የዲጂታል ቤተመጻህፍት አገልግሎት ተማሪዎች በመማሪያ ግብዓቶች እጥረት የሚያጋጥማቸውን ችግር የሚፈታና ተወዳዳሪዎች የሚሆኑበትን መደላድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

በድጋፉ ርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ የዞኖቹ ዋና አስተዳዳሪዎችና የትምህርት ጽሕፈት ቤቶች ኃላፊዎች ተገኝተዋል።