ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ 3 ሺህ 375 ዜጎችን የጤና መድህን ተጠቃሚ የሚያደርግ ገንዘብ ለገሰ

65

ሐረር ፤ ጥር 14/ 2014(ኢዜአ) ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በሐረሪ ክልል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ 3 ሺህ 375 ዜጎችን ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተጠቃሚ የሚያደርግ 2 ሚሊየን ብር ለገሰ።

የተለገሰውን ገንዘብ የተረከቡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር  አቶ ኦርዲን በድሪ እንደተናገሩት፤የክልሉ መንግስት የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት እየሰራ ነው።

በክልሉ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ማዳረስ መሆኑን አመልክተው፤ በዚህም ላይ  የክልሉ መንግስት በስፋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ለመጥቀም የተጀመረው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና አገልግሎት ስራም አበረታች ውጤት እያሳየ ይገኛል ነው ያሉት።

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲም ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ አቅመ ደካማ የማህበረሰብ ክፍሎች አገልግሎቱን እንዲያገኙ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዩኒቨርሲቲው ከክልሉ መንግስት ጋር በሁሉም መስክ የሚያደርገውን የተቀናጀ ስራም ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሚስራ አብደላ በበኩላቸው፤ የጤና መድህን ፕሮግራም ለአቅመ ደካማ ወገኖች የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ በማድረግ የመደጋገፍ ባህል እያሳደገ ይገኛል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የለገሰው 2 ሚሊዮን ብር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል ዩስፍ ፤ የተለገሰው ገንዘብ አቅም ደካማ ዜጎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል።

በክልሉ የተጀመረው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ዘላቂ ሆኖ እንዲቀጥል እና በአገልግሎቱ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ እንደሚከናወንም ተናግረዋል።

ተቋሙ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና አገልግሎትን ከማሻሻል ባለፈ ከክልሉ ጋር በተለያዩ መስኮች የሚያከናውነውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በሐረሪ ክልል ከ45 ሺህ 539 አባወራዎች የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተጠቃሚ መሆናቸውን ያስታወቁት ደግሞ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኢብሳ ሙሳ ናቸው።

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የለገሰው ገንዘብ 3 ሺህ 375 አቅመ ደካማ አባወራዎችን የማህበረሰብ ጤና መድህን አባል በማድረግ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም