ወጣቶች በጦርነቱ ማግስት ሊከሰቱ የሚችሉ ጫናዎችን በመቀልበስ ረገድ ጉልህ ሚና አላቸው

65

አዲስ አበባ ጥር 14/2014(ኢዜአ) የአገሪቷ ወጣቶች ከጦርነቱ በኋላ ሊከሰቱ የሚችሉ ጫናዎችን በመቀልበስ ረገድ ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን የብልጽግና ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ጽህፈት ቤቱ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ የብልጽግና ወጣቶች ሊግ ስራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ አገር አቀፍ መድረክ እንደሚካሄድ አስታውቋል።

አገር አቀፍ መድረኩ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በአዳማ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ አክሊሉ ታደሰ መድረኩ ከሁሉም ክልሎች በሚውጣጡ የወጣቶች ሊግ ስራ አስፈጻሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ የሚካሄድ ነው ብለዋል።

በመድረኩ ከመደበኛ የወጣቶች ሊግ ስራዎች በተጨማሪ በተካሄደው የህልውና ጦርነት የወጣቶች ሚና እና መዋቅሩ ያከናወናቸው ተግባራት ግምገማ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ከሕልውና ጦርነቱ ጋር ተያይዞ በአገሪቷ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች እና ፖለቲካዊ መዛነፎች ሊመጡ እንደሚችሉ ይታሰባል ያሉት ሃላፊው ወጣቶች ጫናዎቹን በመቀነስ ረገድ ሚናቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በተለይም ኢኮኖሚው እንዲያገግም ወጣቶች ከመንግስትና ከሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመቀናጀት በተደራጀ መንገድ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

በመሆኑም የጦርነቱ የድል ማግስት ጉዞ ቅኝት መደረግ በሚገባቸው አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከወጣቶች ጋር ምክክር ይደረጋል ብለዋል።  

አቶ አክሊሉ የወጣት ሊጉ "መቶ ለወገኔ" በሚል ዘመቻ ለመከላከያ ሠራዊት ያሰባሰበውን ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ እንደሚያስረክብም ተናግረዋል።

የብልጽግና ወጣቶች ሊግ በአገሪቷ ከ3 ሚሊዮን 417 ሺህ በላይ አባላት ያሉት ሲሆን በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ይሰራል።

በሕልውና ጦርነቱ ለመከላከያ ሠራዊት እና ለዘማች ቤተሰቦች ድጋፍ በማድረግ፣ በዲፕሎማሲው መስክ የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በማስረዳት፣ ኅብረተሰቡን በማስተባበር አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅ ተግባራት ተሳትፎ ማድረጉንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም