የአሸባሪው ሸኔ የጥፋት ድርጊትን ለመመከት የበኩላችንን እየተወጣን ነው – ወጣቶች

161

ግምቢ ፤ ጥር 14/2014(ኢዜአ) አሸባሪው ሸኔ በሰውና ንብረት ላይ የሚፈጽመውን የጥፋት ድርጊት ለመመከት የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን በምዕራብ ወለጋ ዞን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች ገለጹ።

ወጣቶቹ ፤  የአሸባሪ ቡድኑን አስነዋሪ ተግባር ለማስቆም ከመንግስት ጎን በመሆን እንደሚደግፉ ነው ያመለከቱት።

ቡድኑ አሁን ላይ ተስፋ በመቁረጥ ሰዎችን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ እየገደለና መሰረተ ልማቶችን እያወደመ መሆኑ እንዳስቆጣቸው በመግለጽ የጥፋት ድርጊቱን አውግዘዋል፡፡

ወጣቱን እያሳሳተ መጠቀሚያ በማድረግ የአሸባሪው ህወሓትን ሀገር የማፍረስ ዓላማ ለማሳካት ቢሯሯጥም እንደማይሳካለት ወጣቶቹ ገልጸዋል።

ከወጣቶቹ መካከል ዮናስ ሰለሞን፤ አሸባሪው ሸኔ የነገ ተስፋ የሆኑ ታዳጊዎችን መጠቀሚያ አድርጎ በዞኑ አንዳንድ አካባቢዎች ንጹሃንን በመግደል ጉዳት ሲያደርስ እንደቆየ አውስቷል።

በመንግስትና ህዝብ ገንዘብ፣ ጉልበትና እውቀት ተሳትፎ የተገነቡ መሰረተ ልማቶችን እያፈረሰ ጭምር መቀጠል ስለሌለበት የጥፋት ተግባርን በመመከት ለማስቆም ከፀጥታ አካል ጋር በመሆን የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ነው ያመለከተው።

ወጣት ባልቻ አበበ በበኩሉ፤ የአሸባሪው የሸኔን አፍራሽ ድርጊት ለመከላከል ለጸጥታ አካል በመጠቆም እየደገፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የአሸባሪው ህወሓት ተላላኪ የሆነው ሸኔ በኦሮሞ ህዝብ ስም እየተንቀሳቀሰ ኦሮሞ እየበደለ በመሆኑ ህብረተሰቡ እንቅስቃሴውን በመከታተል ለጸጥታ አካላት መጠቆም አለበት ብሏል ወጣቱ።

አሸባሪው ሸኔ ከማህበረሰቡ ባህልና እሴት ባፈነገጠ መልኩ ሰላማዊ ሰው እየገደለና ንብረት እያወደመ መቀጠል እንደሌለበት የተናገረው ደግሞ ወጣት ታረቀኝ ቤኛ ነው።  

ቡድኑ በኦሮሞስም ይንቀሳቀስ እንጂ የኦሮሞ ህዝብ ጠላት መሆኑን በተግባር እያሳየ መሆኑ የጥፋት ድርጊቱ እንደሚያረጋግጥ አመልክቷል።

የአሸባሪውን ድርጊት ለማስቆም በሚደረገው ትግል ከመንግስት ጎን በመሆን የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግሯል።፡፡

የምዕራብ ወለጋ ዞን የአስተዳደርና የፀጥታ ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ሙላቱ ዲንሳ በበኩላቸው፤ አሸባሪው ሸኔ በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው ግፍና መከራ ተቀምጠን የምናይበት ጊዜ አይደለም ብለዋል።

በዞኑ አንዳንድ አካባቢዎች የሽብር ቡድኑን  እንቅስቃሴ በመከታተል ለጸጥታ አካል መረጃ በመስጠት በተለይ ወጣቶች እያደረጉት ያለው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

የአሸባሪውን ሸኔ ግብረ አበሮች እንቅስቃሴ እየተከታተሉ ወደ ህግ እንዲቀርቡ እየሰሩ መሆኑን አቶ ሙላቱ አስታውቀዋል።