በኦሮሚያ ሁሉም ከተሞች ከነገ ጀምሮ የማስ ስፖርት ይካሄዳል

169

አዲስ አበባ ፣ ጥር 14/2014(ኢዜአ) በኦሮሚያ ሁሉም ከተሞች ከነገ ጀምሮ በወር አንድ ጊዜ የማስ ስፖርት እንደሚካሄድ የክልሉ የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

ነገ የሚጀመረውን ማስ ስፖርት አስመልክቶ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት እና ጤና ቢሮ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሪት ሳሚያ አብደላ እንደገለጹት ነገ ከ5 ሺህ በላይ ሰዎች የሚሳተፉበት የማስ ስፖርት አዳማ ላይ ይካሄዳል።

ማስ ስፖርቱ ወር በገባ በሁለተኛው እሁድ በሁሉም የክልሉ ከተሞች እንደሚካሄድም ገልጸዋል።

የማስ ስፖርት ማዘውተር ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ በተጨማሪ የኅብረተሰቡን ግንኙነትና አብሮነት ይበልጥ ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።

በማስ ስፖርት የሚሳተፉ ሰዎች ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ርቀታቸውን በመጠበቅ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ያሉት ደግሞ የጤና ቢሮ ኃላፊው ዶክተር መንግስቱ በቀለ ናቸው።

ዶክተር መንግስቱ በማስ ስፖርት መሳተፍ በርካታ የጤና እና ማኅበራዊ ፋይዳዎች እንዳሉት ጠቅሰዋል።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል፣ ተላላፊ በሽታዎችን ለመቋቋምና በቶሎ ለማገገም እንደሚያግዝም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በከተሞች የሚኖሩ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችም እየተስፋፉ በመሆኑም ኅብረተሱቡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን መልመድ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ጤናማ አመጋገብ መከተልና ከተለያዩ ሱሶች በመራቅ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችንም መከላከል ይቻላል ብለዋል።

በማስ ስፖርት ላይ የሚሳተፉ ሰዎች ለሌላ ጉዳት እንዳይጋለጡ በአቅማቸው ልክ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ አለባቸው ብለዋል ዶክተር መንግስቱ።