የሠብዓዊ መብት ሕጎችን በመጣስ የሚታወቀው አሸባሪው ህወሓት በሠብዓዊ ድጋፍ ስም የፖለቲካ ቁማር ጨዋታውን ቀጥሎበታል

199

አዲስ አበባ፣  ጥር 14/2014 (ኢዜአ) የሠብዓዊ መብት ሕጎችን ባለማክበር የሚታወቀው አሸባሪው ህወሓት በሠብዓዊ ድጋፍ ስም የፖለቲካ ቁማር ጨዋታውን መቀጠሉን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ተናገሩ።

ኮሚሽነሩ በክልሉ ከዚህ ቀደም የተለያየ ድጋፍ ከመደረጉ ባሻገር አሸባሪ ቡድኑ ወረራ በፈጸመበት ወቅት ኮምቦልቻ ካለው የኮሚሽኑ መጋዘንና ከአጋር አካላት 100 ሺህ ኩንታል እህል መዝረፉንም ተናግረዋል።

ኮሚሽነር ምትኩ ለኢዜአ እንዳሉት፤ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአፋርና አማራ ክልል ወረራ በፈፀመበት ወቅት ካደረሰው ሠብዓዊ ጉዳት ባሻገር ከፍተኛ ዝርፊያና ውድመት አድርሷል።

የወደሙ መሰረተ ልማቶችና ተቋማትን መልሶ በመገንባት ሥራ ለማስጀመር ኢትዮጵያዊያን እየተረባረቡ መሆኑንም ገልጸዋል።

ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች አቅም በፈቀደ መጠን የሠብዓዊ ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን ያብራሩት ኮሚሽነሩ መንግስት ወደ ትግራይ ክልልም የሠብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

ነገር ግን መንግስት ወደ ትግራይ ክልል መድኃኒት እንዲሁም ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች እንዳይገቡ ከልክሏል በሚል በአሸባሪ ቡድኑና በደጋፊዎቹ የሐሰት መረጃ እየተነዛ መሆኑን ጠቁመዋል።

አሸባሪው ህወሓት እንዲህ አይነቱን ሀሰተኛ ውንጀላ ከማቅረብ ይልቅ በሠብዓዊ ድጋፍ ስም የሚጫወተውን የፖለቲካ ቁማር ትቶ ለሠብዓዊ መብት ሕጎች ተገዥ መሆን ይገባዋል ብለዋል።    

ከዚህ ቀደም ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ጋር ውል ተፈራርመው እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ክልል የገቡ ከ1 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን በማስቀረት ለታጣቂ ማመላለሻነት እየተጠቀመበት መሆኑን አስረድተዋል።

መንግስት ዜጎች ሠብዓዊ ድጋፍ ሊያገኙ የሚችሉባቸውን የተለያዩ አማራጮች ለመከተል ብዙ ርቀት መጓዙንም ተናግረዋል።  

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም የአጋር አካላት ኃላፊዎች ባሉበት በአፋር በኩል እርዳታ የማስገባት ሂደቱ ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ጉዳይ ላይ ከአንድ ወር በፊት ውይይት መደረጉን አስታውሰዋል።

ውይይቱን ተከትሎ እስካሁን ባለው ሂደት ከዓለም ምግብ ፕሮግራም በስተቀር የመጣ ድጋፍ ሰጪ አለመኖሩን አንስተዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ሆን ብሎ ትንኮሳ በመፈጸምና መንገድ በመዝጋት የሠብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርስ በማድረግ መንግስት ላይ ጫና ለመፍጠር አስቦ እየሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በአብዓላ መስመር ባደረገው ትንኮሳ ዜጎች መፈናቀላቸውን በማሳያነት ጠቅሰው፤ የዓለም አቀፍ ተቋማት ህወሓት ዓለምአቀፍ የሠብዓዊ መብት ህግን እንዲያከብር ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

ኮሚሽነር ምትኩ አሸባሪ ቡድኑ ኮምቦልቻ ካለው የኮሚሽኑ መጋዘንና ከአጋር አካላት 100 ሺህ ኩንታል እህል ዘርፎ መውሰዱንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በአፋር መስመር ለወራት የሚበቃ እርዳታ ቀደም ብሎ መግባቱን አስታውሰው የአሸባሪ ቡድኑ መሰረተ ቢስ ክስና ውንጀላ ሌላ መስመር ለማስከፈትና በአየር ድጋፍ ስም አገርን የሚጎዳ ስራ ለመስራት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

አሸባሪ ቡድኑ የትግራይ ሕዝብ ጠላት መሆኑን ዕድሜያቸው ያልደረሱ ህፃናትን ለጦርነት በማሰለፍ ጭምር ማሳየቱን አንስተው፤ ትንኮሳውን ያደረገውም ለትግራይ ክልል በማሰብ አለመሆኑን አስረድተዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም መንግስት የሠብዓዊ ድጋፍ እንደከለከለ አስመስለው ያቀረቡትን ሐሰተኛ መረጃ በተመለከተ መንግስት ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት በአብዓላ በኩል ስላስገባቸው የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያዎች ዝርዝር መረጃ ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል ብለዋል።

ለአማራና አፋር ክልል ድጋፍ ተደርጎ ትግራይ ቸል ተብሏል የሚል ሐሰተኛ መረጃ ቢሰራጭም የዓለም ጤና ድርጅት ለክልሎቹ ያቀረበው ድጋፍ ዝርዝር የሚታወቅ በመሆኑ ይህም በተመሳሳይ ለሕዝብ የሚገለፅ መሆኑን ተናግረዋል።

የአንድ ዓለምአቀፍ ድርጅት መሪ በአገር ውስጥ ጉዳይ ገብቶ የሚናገርበት ምንም ሥልጣን ባለመኖሩ የሾመው አካል ተጠያቂ ማድረግ አለበትም ብለዋል።

በተለያዩ ጊዜያት ያለውን እውነታ ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ ሲሰራ እንደነበር አንስተው፤  በትግራይ ክልል ስለተደረገው ሠብዓዊ ድጋፍ በተመለከተ ለዓለምአቀፍ ተራድኦ ድርጅትና አጋር አካላት ተወካዮች ገለፃ መደረጉን ጠቁመዋል።

አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከሚያደርጉት ጫና ባልተናነሰ በሠብዓዊ ድጋፍ ሰበብም ጫና እንደሚያሳድሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን መንግስት ጥረት በተመለከተ እውነቱን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማስረዳት ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ።