የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የ3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

134

አዲስ አበባ፣  ጥር 14/2014(ኢዜአ) የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሠራተኞችና የአመራር አባላት ለአገር መከላከያ ሠራዊት የሶስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ፡፡

ድጋፉን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል እንደሻው ጣሰው ለመከላከያ ሠራዊት ዋር ኮሌጅ አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሀብታሙ ጥላሁን አስረክበዋል።

ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራሉ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ተቋሙ አገር የማዳን ስራው ስኬታማ እንዲሆን የተቀላጠፈ መረጃ በማቅረብ  ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል።

ለመከላከያ ሠራዊት የተደረገው የገንዘብ ድጋፍ የመጀመሪያ ዙር መሆኑን ገልጸው፤ የተቋሙ ሠራተኞች ለሠራዊቱ ያላቸውን አጋርነት ለመግለጽ የተደረገ ነው ብለዋል።

በአገሪቷ የተሟላ ልማትና ሠላም ለማስገኘት በሚከናወኑ ተግባራት ሁሉ የመሪነት ሚናቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የመከላከያ ዋር ኮሌጅ አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ሀብታሙ ጥላሁን የመከላከያ ሠራዊቱ በስኬት እንዲጓዝ የኅብረተሰቡ ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ያደረገው የገንዘብ ድጋፍም የሠራዊቱን ሞራል ይበልጥ የሚያነሳሳና ለድል አድራጊነት የሚያበቃ መሆኑን በመግለጽ ምስጋና አቅርበዋል።  

ተቋሙ ቀደም ሲልም በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ570 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️