የዓባይ ወንዝ መነሻን ለቱሪዝም መዳረሻነት ለማዋል ይሰራል— ዶክተር ይልቃል ከፋለ

204

ፍኖተ ሰላም ጥር 13/2014 (ኢዜአ) -የዓባይ ወንዝ መነሻን በማልማት ለቱሪዝም መዳረሻነት ለማዋል በትኩረት እንደሚሰራ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አስታወቁ።

የታላቁ ዓባይ ወንዝ መነሻ በሆነው ሰከላ ወረዳ የግዮን በዓል ዛሬ ለ4ተኛ ጊዜ ተከብሯል።

በበዓሉ አከባበር ላይ የተገኙት ርዕስ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ “ዓባይ ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ የታወቀ ውሃ ነው” ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው “ስለ አባይ ወንዝ ስናነሳ ባህልም፣ ሀብትም፣ ቅርስም መሆኑን መገንዘብ ይገባናል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን  የወንዙ መነሻ እንዳይጠፋና በቅርስነት ለትውልድ እንዲተላለፍ እያደረገች ያለችው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልፀዋል።

“የክልሉ መንግስት የወንዙ ዳርቻ እንዲለማ፣ ባህሉ እንዲሰፋና የዓባይ ወንዝ መነሻ የሆነው ቦታ በአገር ውስጥና በውጭ ቱሪስቶች እንዲጎበኝ አበክሮ ይሰራል” ሲሉ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያውያንን ኑሮ ለማሻሻል የቱሪዝም ዘርፉን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመው መንግስት የግዮን በዓልን ሁሉም እንዲያውቀው የቻለውን ያህል እንደሚሰራ ተናግረዋል።

“ዓባይን ለራሳቸው ብቻ መጠቀም የሚፈልጉ አገራት የእርስ በርስ ልዩነታችንን በማስፋት እንዳንጠቀም እየጣሩ ስለሆነ ይህን በጋራ ማክሸፍ ይግባል” ሲሉም ዶክተር ይልቃል አመልክተዋል።

ወንዙ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካም ወሳኝ የዲፕሎማሲ አጀንዳ እንደሆነ ጠቁመው ሌሎች በወንዙ መጠቀም የሚችሉት አመንጪዋ ኢትዮጵያ ስትጠቀም ብቻ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

“ከድህነት ለመውጣት በኢትዮጵያውያን ትብብር በዓባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ካለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተጨማሪ ወንዙን ለቱሪዝም መዳረሻ ማዋል አለብን” ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ከልማት ስራ ጎን ለጎን ክልሉን ሰላም የሰፈነበትና የጥይት ድምጽ የማይሰማበት ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ዶክተር ይልቃል አስታውቀዋል።

“የግዮን በዓል መከበር ከጀመረ ወዲህ የወረዳችን የልማት ጥያቄዎች መመለስ ጀምረዋል” ያሉት ደግሞ የሰከላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በላይነህ አማረ ናቸው።

ከቲሊሊ–ሰከላ የሚወስደውን መንገድ ወደ አስፋልት ለማሳደግ ሥራ መጀመሩንና የሆቴልና መሰል ኢንቨስትመንት ጥያቄዎች በባለሀብቶች እየቀረቡ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ዋና አስተዳዳሪው አክለውም “ከወንዙ የምናገኘውን የሩቅ ዕድገት አስበን ሁላችንም በልማቱ ልንረባረብ ይገባናል” ብለዋል።

“በወንዙ የህዝባች ኑሮ እንዲቀየር ዘላቂነት ያላቸው ሥራዎችን እንሰራለን” ሲሉም አመለክተዋል።

“ከወንዙ የሚገኘውን ማር ለመጠቀም ሁሉንም ወደ ጎን በመተው እንደንብ ያለዕረፍት መስራት ይገባል” ያሉት ደግሞ የምዕራብ ጎጃም ዞን ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዘካሪያስ ናቸው።

በስነ ስርዓቱ ላይ ከፌደራል፣ ከክልል፣ ከዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን፣ ጥናታዊ ጽሁፎችም በምሁራን ቀርበው ውይይት ተካሄዷል።