የአካል ድጋፍ አቅርቦትን በማሻሻል አካል ጉዳተኞች ለሀገራዊ እድገት ያላቸውን አበርክቶ ማሳደግ ይገባል

185

አዲስ አበባ ፣ ጥር 13/2014(ኢዜአ)  የህክምናና የአካል ድጋፍ አገልግሎቶችን በማሻሻል አካል ጉዳተኞች ለሀገር እድገት ያላቸውን ሁለንተናዊ ሚና ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ።

የጤና ሚኒስቴር የአካል ድጋፍ  ከሚያመርቱና ጥሬ እቃዎችን ከሚያቀርቡ አካላት ጋር ዘርፉን ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርጓል፡፡

በዚሁ ወቅት በሚኒስቴሩ የህክምና ተሀድሶ ዳይሬክተር ዶክተር አባስ ናስር እንዳሉት የህክምና መስጫ አቅርቦት እና ፍላጎት ዝርዝር መረጃዎች ቢኖሩም የህክምና ተሀድሶን አለማካተታቸው አካል ጉዳተኞች ተገቢውን የአካል ድጋፍ እንዳያገኙ አድርጓል፡፡

ከዚህ ቀደም የአካል ድጋፍ አገልግሎቶችን የተመለከቱ ስራዎች በሀላፊነት ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መሰጠታቸው በተለይ ጤና ተኮር የሆኑ ሙያዊ ስራዎች ላይ ተጽእኖ መፍጠሩን ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የህክምናና የአካል ድጋፍ አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ ለጤና ሚኒስቴር መሰጠታቸውን አስታውሰው የአካል ጉዳተኞችን ጤና በማሻሻል በተሰማሩበት የስራ መስክ ውጤታማ ማድረግ የሚያስችል የጤና ፖሊሲ መቀረጹን ተናግረዋል፡፡

የአካል ድጋፍን ተደራሽ የሚያደርግ የማምረቻ ማዕከል መገንባቱንና ብቁ የሰው ሀይል ለማፍራት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል ፡፡

ህክምናው በመንግስትና በግል ህክምና ተቋማት እንደሚሰጥና ለአብነትም በጎንደር፣ ሀረር፣ ጋምቤላ ሆስፒታል ተደራሽ ለማድረግ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡

ቼሻየር ኢትዮጵያ የተሰኘው በጎ አድራጊ ተቋም አነስተኛ ገቢ ላላቸው አካል ጉዳተኞች ላለፉት ስልሳ አመታት የህክምናና የአካል ድጋፍ እየሰጠ እንደሚገኝ የድርጅቱ ዳይሬክተር ፋሲል አየለ ገልጸዋል፡፡  

የአካል ድጋፍ ለሚያመርቱና ህክምና ለሚሰጡ ተቋማት ትኩረት ባለመሰጠቱ በዘርፉ በቂ የሰው ሀይል ማግኘትና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ  እንቅፋት መፍጠሩን አስታውሰዋል፡፡  

የአካል ጉዳተኞችን መብትና ማህበራዊ አቅሞች ለመገንባት የተደረገውን ጥረት ያህል የህክምና ተሀድሶ አገልግሎቱ አለመስፋቱ አካል ጉዳተኞች ለሀገር የሚኖራቸውን ዘርፈ ብዙ አበርክቶ እንደቀነሰው አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ልማት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ለጋሱ ልኡልሰገድ በበኩላቸው “አካል ጉዳት በአካል ጉዳተኞች  ላይ ከሚያሳርፈው ጉዳት በላይ የሚኖሩበትና  የሚሰሩበት አካባቢ እንዲሁም የማህበረሰቡ ግንዛቤ ከፍተኛ ጫና ይፈጥርባቸዋል”  ብለዋል፡፡

የአካል ድጋፍ ያለ ማንም እርዳታ ተንቀሳቅሰው ምርታማ እንዲሆኑና ጉዳቱ የፈጠረባቸውን ተጽእኖ ስለሚያካክስላቸው ለተደራሽነቱ መስራት እንደሚገባም ዳይሬክተሩ አመልክተዋል፡፡

የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ለአካል ጉዳተኞች ብቻ የሚተው ባለመሆኑ የሚመለከተው አካልና ህብረተሰቡ በመተጋገዝ  ያላቸውን እውቀትና ልምድ ተጠቅመው ለሀገር እድገት የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ መደላድል መፍጠር  ይገባል ነው ያሉት፡፡