በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች አገራቸውን በማስተዋወቅ ለልማቷ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል

170

አዲስ አበባ ፣ ጥር 13/2014(ኢዜአ)   በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች የአገራቸውን የተፈጥሮ ፀጋና ገጽታ በማስተዋወቅ፤ ለቱሪዝም እድገት ብሎም ለልማት አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚገባቸው ተገለፀ።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወጣት ዳያስፖራዎች ያላቸውን እውቀት፣ ተሞክሮ፣ ሃብትና ቴክኖሎጂ በመጠቀም ከአገር ቤት ወጣቶች ጋር በመጣመር ለአገር እድገትና ለውጥ እንዲሰሩ የሚያነሳሳ የመክፈቻና የእውቅና መርሃ ግብር አካሄዷል።

በአገር ውስጥ ያሉና ዳያስፖራ ወጣቶችን በማቀናጀት የሚሰራው የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ወጣቶች ኅብረትም ወጣቶች በአገር ግንባታና ልማት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ማድረግ እንደሚገባ አስታውቋል።

በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ተወልደው ያደጉ ወጣት ዳያስፖራዎችን ከአገር ቤት ወጣቶች ጋር በአካልና በማኅበራዊ ድረገጽ እንዲማማሩ በማድረግ የአገር ፍቅር እንዲኖራቸው ማስቻልና በልማትም አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ የኅብረቱ ዓላማ መሆኑ ተገልጿል።

የኅብረቱ መስራችና ፕሬዚዳንት ወጣት ቢንያም ጌታቸው ወጣቶች በተለይም ወቅቱ በሚጠይቀው የቴክኖሎጂ ዘመን በዲፕሎማሲና በገጽታ ግንባታ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ለማድረግ ወጣቶቹን ማቀናጀት ያስፈልጋል ብሏል።

በተለይም በውጭ ያሉት ወጣቶች ስለ አገራቸው የተፈጥሮ ፀጋና ገጽታ ለዓለም ማኅበረሰብ እንዲያስተዋውቁ  በማድረግ ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ በማነሳሳት ለቱሪዝም እድገት ሚናቸውን እንዲወጡ ማድረግ እንደሚቻል አንስቷል።

በአገር ውስጥ ያሉት ደግሞ የሚመጡትን ቱሪስቶች በማስጎብኘት የስራ ዕድል ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ እንደሚፈጠርና በዚህ ሂደትም የአገሪቷ ቱሪዝም እንዲያድግ ማድረግ እንደሚቻል አስረድቷል።

ይህ በድምሩ አገር ከቱሪዝም ልማት ተጠቃሚ እንድትሆን በማድረግ ለኢኮኖሚዋ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ነው የገለፀው።

የዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እንድሪስ፤ በአገር ቤት ያሉ ወጣቶችን በውጭ ካሉት ዳያስፖራ ወጣቶች ጋር በማስተሳሰር አገር ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚ የምትሆንበትን መንገድ ማመቻቸት ያሻል ብለዋል።

ይህን እውን ለማድረግም ኤጀንሲው ከኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ወጣቶች ኅብረት ጋር በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የ”በቃ” መስራች ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊን ጨምሮ በርካታ ዳያስፖራ ወጣቶች ታድመዋል።