የፍትህ አገልግሎቱን በተሻለ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው

211

ጥር 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፍትህ አገልግሎትን በተሻለ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ፍትህ ሚኒስቴር ገለጸ።

የመጀመሪያው ‘የኢትዮጵያ ጠበቆች ማሕበር’ ጉባኤ ጥር 15 ቀን 2014 ይካሄዳል።

ጉባኤውን በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የፍትህ ሚኒስቴር የመንግስት ህግና ፍትህ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለምአንተ አግደው፤ የፍትህ ሥርዓቱን የሚያሻሽሉ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

በፍትህ ሥርዓት ውስጥ ጉልህ ሚናና ድርሻ ካላቸው የህግ አካላት ጠበቆች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ ነው ያሉት።

እነዚህ ሙያተኞች ግለሰቦችን፣ ድርጅቶችን እንዲሁም አብዛኛውን የሕብረተሰብ ክፍል ወክለው በፍርድ ቤት የህግ ክርክር የሚያደርጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ይህም በመሆኑ የፌዴራል ጥብቅና አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደር አዋጅ አዳዲስ ጉዳዮችን አካቶ ባለፈው ዓመት ጸድቋል ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።

በአዋጁ መሰረት ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ያልነበረ የጠበቆች ማሕበር እንዲቋቋም ተደርጓል ብለዋል።

አዋጁ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማንኛቸውም የፌዴራል የጥብቅና ፈቃድ ያላቸው ጠበቆች ወይም የጠበቃ ድርጅቶች የማሕበሩ አባል እንዲሆኑ በአስገዳጅነት ማስቀመጡን ተናግረዋል።

የዚህ ማሕበር አባል ያልሆኑ አካላት የጥብቅና አገልግሎት መስጠት እንደማይችሉም እንዲሁ።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ ይህ እንዲሆን የተደረገው የፍትህ አገልግሎትን በተሻለ መልኩ ለመስጠትና የደንበኞችን መብትና ጥቅም ለማስከበር ነው።

ጠበቆችም ቢሆኑ በማሕበራቸው አማካኝነት አቅማቸውን መገንባት እንዲችሉና ሙያዊ ስነ-ምግባርን ጠብቀው እንዲሰሩ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።

በጥቅሉ አዋጁ የፍትህ ሥርዓቱንና የፍትህ አገልግሎቱን ወደ ተሻለ መንገድ የሚወስድ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአዋጁ መሰረት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ጠበቆች ማሕበር ከነገ በስቲያ በሚያደርገው የመጀመሪያ ጉባኤ ሰባት ሥራ አስፈጻሚዎችን፣ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት እንደሚመርጥ ጠቁመዋል።

የፍትህ ሚኒስቴር የጠበቆች ማኅበርን ጨምሮ የህግ አገልግሎቱን ለማሻሻል የሚያግዙ የሙያ ማሕበራትን እንደሚደግፍ አቶ ዓለምአንተ ገልጸዋል።