ኅብረተሰቡ ለገቢ ማሰባሰቢያ በተዘጋጀው የእግር ኳስ ጨዋታ እየተዝናና ወገኑን እንዲረዳ ጥሪ ቀረበ

68

አዲስ አበባ ፣ ጥር 13/2014(ኢዜአ)  ኅብረተሰቡ በኢትዮጵያ ዳያስፖራና የአገር ቤት ቡድን የቀድሞ ታዋቂ ተጫዋቾች መካከል በሚካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ የእግር ኳስ ጨዋታ እየተዝናና ወገኖቹን እንዲረዳ ጥሪ ቀረበ።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራና የአገር ቤት ቡድን የእግር ኳስ ጨዋታው ከነገ በስትያ እሁድ ከቀኑ 7፡00 ሠዓት ጀምሮ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚካሄድ የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ገልጸዋል።

ጨዋታው በዋናነት በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት ቢዘጋጅም ጎን ለጎን በዳያስፖራውና በአገር ውስጥ በሚኖረው ማኅበረሰብ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር መዘጋጀቱን አስተባባሪው ማስተር ሄኖክ መገርሳ ተናግረዋል።

እሑድ ጥር 15 ከቀኑ 7፡00 ሠዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲዮም በታዳጊዎች እንዲሁም በኮሜዲያንና በደጋፊዎች መካከል የእግር ኳስ ግጥሚያ እንደሚደረግ ተገልጿል።

ጨዋታውን ለመታደም የአገር ውስጥ ደጋፊዎች ለክቡር ትሪቡን 1 ሺህ ብር፣ ለጥላ ፎቅ 500 ብር ለቀሩት ቦታዎች 100 ብር የመግቢያ ዋጋ ነው።

ዳያስፖራ ተመልካቾች ክቡር ትሪቡን 100 ዶላር፣ ጥላ ፎቅ 75 ዶላርና ሌሎች ቦታዎች 50 ዶላር መግቢያ የሚከፍሉ መሆኑን አስተባባሪዎቹ አስታውቀዋል።

የመግቢያ ትኬቱ በሁሉም የንግድ ባንክ ቅርንጫፎችና በአይዞን ኢትዮጵያ የገቢ ማሰባሰቢያ መተግበሪያ ኦን ላይን እንደሚሸጥም አቶ ቴድሮስ ባጫ ተናግረዋል።

የእግር ኳስ ውድድሩን በየዓመቱ ለማካሄድ እንደታሰበም አስተባባሪዎቹ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ታዳጊ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን በማብቃት ተጫዋቾችን በብዛት ለማፍራት የሚረዱ ፕሮግራሞች በቀጣይ መታሰባቸውን ከመግለጫው መረዳት ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም