ተጋቢዎች በሠርግ ዝግጅታቸው በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻቸውን እንዲያስታውሱ ጥሪ ቀረበ

105

ጥር 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ጋብቻቸውን የሚፈጽሙ ሙሽሮች በሠርግ ወጪያቸው የአገሪቷን ወቅታዊ ሁኔታና የተቸገሩ ወገኖችን ታሳቢ እንዲያደርጉ የሃይማኖት አባቶች መከሩ።

ወርሃ 'ጥር' በተለየ ሁኔታ ሙሽሮች የጋብቻ ስነ-ስርዓታቸውን የሚፈጽሙበትና ጎጆ የሚቀልሱበት፤ ተከታታይ ሃይማኖታዊ በዓላትም የሚከበሩበት ነው።

የሠርግ ስነ ስርዓትና ክብረ በዓላቱም ዘመድ አዝማድ፣ ጓደኛሞችና ወዳጆች የሚገናኙባቸው፣ የሚጠያየቁባቸውና የሚገባበዙባቸውም ናቸው።

ሙሽሮች ሠርጋቸውን ለመደገስ የሚመርጡት ወርሃ ጥር ከፍተኛ ወጪ የሚወጣበትን እንደሆነም ይነገራል።

ወቅቱ ኢትዮጵያ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በኢኮኖሚዋ ላይ ያደረሰውን ጫና ለመቋቋም የተለያዩ አመራጮችን እየተገበረች ያለችበት እንደሆነም እሙን ነው።

ኢዜአ ወቅታዊውን አገራዊ ሁኔታና በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ከሙሽሮችና የሠርግ ወጪያቸው ጋር አያይዞ የሃይማኖት አባቶችን አነጋግሯል።

የሃይማኖት አባቶቹ የዘንድሮን የሠርግም ይሁን የበዓላት ወጪ ቀነስ በማድረግ በጦርነቱ የተጎዱትን መርዳት፣ ከቀያቸው የተፈናቀሉትንም ወደቀደመ ኑሯቸው መመለስ ይገባል ይላሉ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት የቅርስ፣ ላይብረሪና ሙዚየም ዋና ኃላፊ ዶክተር መልዓከ ሠላም አባ ቃለጽድቅ በአገሪቷ የተከሰተው ችግር የአንድ ማኅበረሰብ ወይንም የተወሰኑ አካላት ብቻ ነው ተብሎ አይወሰድም ይላሉ።

ችግሩን አብሮ በማከም ኢትዮጵያን ከገጠማት ችግር ማሻገር ያስፈልጋል ብለዋል።

በጥር ወር ጋብቻቸውን የሚፈጽሙ ሙሽሮችም ሠርጋቸውን ሲፈጽሙ የተፈናቀሉ ዜጎችን በማሰብ እንዲሆን ጠይቀዋል።

ደስታን ከተቸገሩ ጋር ማሳለፍን የሃይማኖቱ አስተምህሮ ያዛል ያሉት ዶክተር መላዕከ ሠላም ተጋቢዎች ቢቻሉ በቃልኪዳን ብቻ አልያም በፈልጉት አማራጭ በቀላሉ በመፈጸም ወጪያቸውን እንዲለግሱም ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የዑላማ ምክር ቤት አባልና የሠላምና እርቅ ዘርፍ ኃላፊ ሼህ መሀመድ ሲራጅም ኢትዮጵያዊያን ለመረዳዳትና ለመደጋገፍ ሩህሩህ ልብ ያላቸው ሕዝቦች ናቸው ሲሉ ይገልጻሉ።

እንደ እርሳቸው ገለጻ በተለይ ችግር በገጠመ ጊዜ መተዛዘን፣ መረዳዳትና መደጋገፍ የግድ እንደሚል አስተምህሮው በጥብቅ ያዛል፤ ይህ ተግባርም በፈጣሪ ፊት ሞገስን ያሰጣል።

በመሆኑም በቅርቡ ሠርጋቸውን ለመደገስ ያቀዱ ጥንዶች ከወጪያቸው ለተጎዱ በማጋራት በዘመናቸው ታሪክ ለመስራትና ለልጆቻቸውም በጎ-ምግባርን ለማስተላለፍ ይህ ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል።

ተጋቢዎች ባላቸው አቅም የተፈናቀሉትን በማሰብ፣ በችግር ላይ ያሉ ወገኖችን የደስታቸው ተካፋይ እንዲሆኑ በማድረግ ታሪክ መስራትና ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ መክረዋል።

አገር ችግር ላይ ስትሆን፣ ዜጎች ድጋፍን ሲሹ ማገዝና መደገፍ የምዕመናን መገለጫ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ቤተክርስቲያን ኅብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻዲቁ አብዶ ናቸው።

እምነት በቃልና በጽሁፍ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ጭምር መሆን አለበት፤ ይህ  በአስተምህሮውም በግልጽ ተቀምጧል ሲሉ ያብራራሉ።

በተጨማሪም የደስታን ጊዜ ከተደሰቱት ጋር ብቻ ሳይሆን ካዘኑትና ከተጎዱት ጋር በማድረግ ሃዘናቸውን ማስረሳትና ማጽናናት ያስፈልጋል ብለዋል።

ፓስተር ጻድቁ ደስታ ሙሉ እንዲሆን፣ የህሊና እርካታ ለማግኘትና የፈጣሪንም ትዕዛዝ ለመፈጸም የተፈናቀሉ ዜጎችን ማገዝና መርዳት ላይ ኃላፊነት መውሰድ ይገባል ሲሉ መክረዋል።

"ኢትዮጵያዊያን ለመስጠት እንጂ ለመለመን እጃቸው ቅርብ አይደለም" ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ላዛሪስት ገዳም አስተዳዳሪ አባ አብነት አበበ ናቸው።

"በፊት ለጋሽ የነበሩ ሰዎችም ጭምር አሁን ባጋጠማቸው ክስተት ምክንያት የወገናቸውን ድጋፍ የሚጠብቁ ሆኗል" ብለዋል።

ሕዝብ ተቸግሮ ተጎድቶ እንዳለ እየታወቀ ደስታን ለብቻ ማሳለፍ በሃይማኖት ታንጾ ከኖረ ሕዝብ የሚጠበቅ ባለመሆኑ ይህ ጊዜ እስከሚያልፍ ደስታን በማቆየት ለተቸገሩ ወገኖች መድረስ የግድ ነው ብለዋል።

መረዳዳትና መደጋገፍ ከጥንት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ኢትዮጵያዊ ባህል ነው ያሉት አባ አብነት በቅርቡ ለመሠረግ ያሰቡ ጥንዶችም በመመካከር ደስታቸውን ከተቸገሩ ወገኖች ጋር እንዲጋሩ ጥሪ አቅርበዋል።

መላው ህዝብ ለመከላከያ ሰራዊቱ እያደረገ ላለው ያልተቋረጠ ድጋፍና ደጀንነት የሃይማኖት አባቶቹ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ይህንን በጎ ተግባር ማስቀጠል የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም