የአፍሪካ ዊልቼር ቅርጫት ኳስ ሻምፒዮን ተካፋይ አገራት አዲስ አበባ እየገቡ ነው

181

አዲስ አበባ ጥር 13/2014(ኢዜአ) በ11ኛው የአፍሪካ ዊልቼር ቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና የሚካፈሉ አገራት አዲስ አበባ እየገቡ መሆኑን የኢትዮጵያ ዊልቼር ቅርጫት ኳስ አሶሴሽን ገለጸ።

የአሶሴሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ሄኖክ ማስረሻ ውድድሩን ለማካሄድ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ውድድሩ ከመጪው እሁድ ጥር 15 ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

አቶ ሄኖክ በውድድሩ ከሚካፈሉ አገራት መካከል የአልጄሪያና የግብጽ ልዑካን አዲስ አበባ መግባታቸውን ተናግረዋል።

ሌሎች ተሳታፊ አገራትም ዛሬ እና ነገ አዲስ አበባ እንደሚገቡ ይጠበቃል ብለዋል።

ውድድሩን የሚመሩ ዳኞች ከሁለት ቀን ቀደም ብለው አዲስ አበባ መግባታቸውንም ነው የተናገሩት።

የውድድሩ በኢትዮጵያ መካሄድ እምቅ አቅም ያላቸው አካል ጉዳተኞችን ለማነሳሳት አስተዋጽኦው የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ውድድሩን እንድታዘጋጅ መመረጧም ለገጽታ ግንባታና ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ያግዛል ብለዋል።

የውድድሩ አሸናፊዎች በዱባይ በሚካሄደው የዓለም ዊልቼር ቅርጫት ኳስ ውድድር አፍሪካን ወክለው የሚሳተፉ ይሆናል።

በዚህ ውድድር በወንዶች ኢትዮጵያ፣ አልጀሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ግብፅ እና ዴሞክራቲክ ኮንጎ፤ በሴቶች ደግሞ ኢትዮጵያ፣ አልጀሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኬንያ ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ የዊልቼር ቅርጫት ኳስ ተጫዋቾች ላለፉት ሶስት ወራት ጠንካራ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸው ተነግሯል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴም ትናንት በልምምድ ቦታ ተገኝተው የቡድኑን አባላት አበረታተዋል።