ከሃምሳ በላይ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የተሳተፉበት 'ኢትዮጵያ የእኛ እናት' የሙዚቃ ክሊፕ ይመረቃል

59

ጥር 13/2014/ኢዜአ/ከሃምሳ በላይ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የተሳተፉበት 'ኢትዮጵያ የእኛ እናት' የተሰኘ የሙዚቃ ክሊፕ በመጪው ጥር 20 በብሔራዊ ቴአትር ለምረቃ ይበቃል።

የመርሃግብሩ አስተባባሪዎች ዛሬ በብሔራዊ ቴአትር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት የሙዚቃ ክሊፑ በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች ገቢ ለማሰባሰብ የተዘጋጀ ነው።

የሙዚቃ ክሊፑን ያቀናበረው ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ የሙዚቃ ክሊፑ የተዘጋጀው በአገር ጉዳይ ሁሉም በሙያው የበኩሉን ድርሻ መወጣት ስላለበት ነው ብሏል።

ከቴአትርና ከፊልም፣ ከሙዚቀኞች፣ ከሠዓሊያንና ከሌሎች የኪነ-ጥበብ ዘርፎች የተውጣጡ ቁጥራቸው ከ50 በላይ ባለሙያዎች በክሊፑ መሳተፋቸውን ገልጿል።

ሙዚቃው የገጣሚ ፍሬዘር አድማሱን 'ኢትዮጵያ የእኛ እናት' የተሰኘ ግጥም መነሻ በማድረግ መቀናበሩንም ተናግሯል።

ሙዚቃው በአብዛኛው የፒያኖ ቅንብር ላይ መሠረት ያደረገ ሲሆን ማሲንቆና ትራምፔት ተካተውበታል።

ዓለም አቀፍ ይዘት እንዲኖረውና ከዘመኑ ጋር እንዲሄድም አንጋፋ የሙዚቃ ባለሙያዎችን ከመረዋ ኳየር ጋር በማጣመር ተዘጋጅቷል።

የኦፔራ ስልትና የሴንፎኒ ኦርኬስትራ ዘውግ ያለው በመሆኑ የተመልካችን መንፈስ ስለሚይዝ የታለመለትን ግብ ለመምታት ያስችላል ብሏል ፒያኒስቱ።

የሙዚቃ ክሊፑ ዳይሬክተር ዳግማዊ ፈይሳ በበኩሉ የሙዚቃ ክሊፑ ሲሰራ የተለያዩ ደረጃዎች እንደነበሩትና  ሦስት ወራትም መፍጀቱን ተናግሯል።

የምረቃ ፕሮግራሙ የመግቢያ ቲኬት 1 ሺህ ብር እንደሆነና በመርሃ ግብሩ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ ለተጎዱ ወገኖች ለማዋል መታቀዱንም ገልጿል።

ዳግማዊ በክሊፑ ምረቃ ዕለት የሙዚቃው አቀናባሪ ፒያኒስት ግርማ ይፍራሽዋ ከሌሎች ሙዚቀኞች ጋር በመሆን የሙዚቃ ሥራውን እንደሚያቀርብም አስታውቋል።

'ኢትዮጵያ የእኛ እናት' የሙዚቃ ክሊፕ የ8 ደቂቃ ከ43 ሰከንድ ፍጆታ እንዳለው ከአስተባባሪዎቹ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም