የህብረቱ መሪዎች ስብሰባ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰኑ የዲፕሎማሲ ስኬት ማሳያ ነው-አቶ ደስታ ሌዳሞ

189

ሐዋሳ፤ጥር 13/2014(ኢዜአ)፡ 35ኛው አፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰኑ የዲፕሎማሲ ስራዎች ስኬታማነት ማሳያ መሆኑን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ተናገሩ ።


ርዕሰ መስተዳደሩ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አሸባሪዎቹ የህወሓትና የሸኔ  ቡድኖች በወሰዱት ተልእኮ የኢትዮጵያን አንድነት በመሸርሸርና ሰላም በማደፍረስ ህልውናዋን  አደጋ ውስጥ ለመክተት ያለ የለሌ ሃይላቸውን ተጠቅመዋል።

ይህንኑ ተከትሎ የተለያዩ ዓለም አቀፍ  ጫናዎችን  ለማድረስ ጥረት መደረጉን አመልክተው፤ 35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በኢትዮጵያ እንዳይካሄድ የተለያዩ ጫናዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን አንስተዋል።

መንግስት፣  በሀገር ውስጥና በውጭው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጫናዎችን ለመቀልበስ  የተቀናጀ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወናቸውን አስታውሰዋል።

የህብረቱ መሪዎች በኢትዮጵያ ጉባኤያቸውን ለማካሄድ የተወሰነው ውሳኔ የዲፕሎማሲ ስኬት መሆኑን ጠቁመው  “ይህም ለኢትዮጵያ የአሸናፊነት ማህተም ነው” ብለዋል።

ጉባኤው አዲስ አበባ ላይ መካሄዱ አፍሪካን  አስመልክቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን እይታ ለማስቀየር የሚረዳና እድል የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል።

በተለይም በጸጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ የውክልና ቦታ እንዲኖራት የተጀመረውን ትግል ወደላቀ ደረጃ የማሸጋገር ዕድል የሚፈጥር ጉባኤ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አፍሪካዊያን ከነጮች የበላይነት ነጻ እንዲወጡና በአንድነት ድምጻቸውን የሚያሰሙበት ህብረት ለማቋቋም የተጀመረው የፓን አፍርካኒዝም እንቅስቃሴ ፋና ወጊ መሆኗን የተናገሩት ደግሞ የሐዋሳ ከተማ ካንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ ናቸው ።

የአፍሪካ ህብረት እንዲመሰረትና የውጭ ጣልቃ ገብነትን በጋራ ለመታገል እንዲቻል የትግል ስልት በመቀየስ ኢትዮጵያዊያን  የቀዳሚነት ሚና መጫወታቸውን አስታውሰዋል።

የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ስብሰባቸውን በአዲስ አበባ ለማድረግ መወሰናቸው ከኢትዮጵያ ጎን መሆናቸውን የሚያሳ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ከአፍርካ ህብረት መስራችነት ባሻገር የአንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራትን ጫናን በመቃወም ለሌሎች ሀገሮችም ምሳሌ አየሆነች መምጣቷን የቅርብ ጊዜ ንቅናቄዎች እንደሚያሳዩ አስረድተዋል።

በጉባኤው የሚሳተፉ የአፍሪካ መሪዎች ህብረታቸውን ከማጠናከር ባለፈ ተጽዕኖዎችን በተደራጀ መልኩ ለመመከት የሚያስችል ወቅቱ የሚጠይቀውን የትግል ስልት ሊቀይሱ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የአፍሪካ ሀገራት ምሁራን ኢትዮጵያ የህብረቱ ዋና መስራችና መቀመጫ ከመሆኗ ባለፈ ሃላፊነቷን በአግባቡ እየተወጣች ስለመሆኑ በጥናት በመታገዝ ለዓለም ሀገራት ማሳየትና ማስተማር እንደሚገባ አመላክተዋል።

በተለይም የአፍሪካ ሀገራት እየደረሰባቸው ያለውን ጫና ለመመከት የሚያስችሉ ስራዎች መጠናከር እንዳለባቸው ረዳት ፕሮፈሰሩ አመልክተዋል ።