የግዮን በዓል በታላቁ ዓባይ ወንዝ መነሻ በሆነችው በሰከላ እየተከበረ ነው

199

እንጅባራ ፤ ጥር 13/2014 (ኢዜአ) የግዮን በዓል ለአራተኛ ጊዜ በዓባይ ወንዝ መነሻ ምንጭ በሆነችው በሰከላ ወረዳ በድምቀት እየተከበረ ነው።

በዓሉ ጥር 13 በወረዳው ዋና ከተማ ግሽ ዓባይ ከአቡነ ዘርዓብሩክ ዓመታዊ የንግሥ በዓል ጋር ተቀናጀቶ ሲከበር እንደቆየ ተገልጿል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ክብረት ሞላ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በዓሉ ከአራት ዓመታት ወዲህ በክልል ደረጃ ዕውቅና ተሰጥቶት እየተከበረ ነው።

በዓሉ በታላቁ አባይ ወንዝ መነሻ ምንጭ መከበሩ ድምቀት እንደሰጠውና የአንድነታችን መገለጫ እየሆነ መጥቷል ናው ያሉት።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መነሻ የአባይ ወንዝ መሆኑን በማስተዋወቅም አካባቢው ትኩረት ተሰጥቶት በመልማት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በዚህም አካባቢው ትኩረት እያገኘ በመምጣቱ የመንገድ መሰረተ ልማት እንዲጀመርና ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችን ለመገንባት ፍላጎት ያላቸውን ባለሃብቶች ስቧል ብለዋል።

አካባቢውን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱን አቶ ክብረት ያመለከቱት።

በዓሉን ለማድመቅም የሩጫ ውድድር፣ የፈረስ ጉግስ እንዲሁም በበዓሉ ዙሪያ ፓናል ውይይት እንደሚካሄድ ታውቋል።

በዓሉ እየተከበረ ያለው የአማራ ክልልና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ባለሀብቶች፣ የእንጅባራና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎችም የማህበረሰብ ክፍሎች በተገኙበት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም