የአርብቶ አደሩ የአኗኗር ዘይቤና ዘመን ተሻጋሪ ልምዶች የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ መገለጫዎችና እሴቶች ናቸው

142

ጥር 13 ቀን 2014 (ኢዜአ)   አርብቶ አደርነት እንደ ሌሎች የአኗኗር ዘይቤዎች ሁሉ አዋጪና ለአገር እድገትና ብልጽግና የጎላ ድርሻ ያለው ነው ሲል የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ 18ኛው የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች ቀን “የአርብቶ አደሩ ልማት ለአገራዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ በአዳማ እንደሚከበር አስታውቋል።

የበዓሉን አከባበር በተመለከተው መግለጫው የኢትዮጵያ “አርብቶ አደሮች የበርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ፀጋዎች ባለቤቶች ናቸው” ብሏል።

የአርብቶ አደሩ የዳበሩ ማኅበራዊ ሃብቶችና ባሕላዊ እሴቶች፤ አደጋ ተቋቋሚ የአኗኗር ዘይቤና ዘመን ተሻጋሪ ልምዶችም የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ መገለጫዎችና እሴቶች መሆናቸውን ጠቅሷል።

በቆላማው የአገሪቷ አካባቢ አርብቶ አደሮች ሰፊውን የግጦሽ መሬት ለዘመናት ባዳበሩት ዘመን ተሻጋሪ አገር በቀል እውቀትና ክህሎት የእንስሳት ተጓዳኝ ሃብቶችን መሠረት አድርገው ይጠቀማሉ፤ ወደ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተደማሪ ሃብትም ይቀይራሉ።

ይሁንና እነዚህ አርብቶ አደሮች በተለያዩ ጊዜያት በተፈጥሮ በሚከሰቱ ችግሮች ተጠቂ መሆናቸውን  መግለጫው አመላክቷል።

በመሆኑም መንግሥትና የልማት አጋሮች የአርብቶ አደሩን የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ልማት ክፍተቶች የሚሞሉ የልማት ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶችን ቀርጸው ሲተገብሩ መቆየታቸውን ጠቅሷል።

ከአገራዊ ለውጡ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው የአስተሳሰብና የአደረጃጀት ለውጥ አርብቶ አደርነት እንደ ሌሎች የአኗኗር ዘይቤዎች ሁሉ አዋጪና ለአገር እድገትና ብልጽግናም የጎላ ድርሻ እንዳለው የታመነበት እንደሆነም መግለጫው ጠቁሟል።

ለመጀመሪያ ጊዜ የአርብቶ አደር ልማት ፖሊሲና ማስፈጸሚያ ስትራቴጂ በመንግስት ፀድቆ ወደ ስራ መገባቱንና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ይህንኑ ለማስፈፀም መቋቋሙንም አትቷል።

የዘንድሮው በዓል በመሠረታዊነት በተፈጥሮ ለሚከሰቱ ችግሮች የመፍትሔ አማራጮችን ከማስቀመጥ ባሻገር መላው አርብቶ አደር ለአገር እድገትና ብልጽግና የበኩሉን ሚና የሚያበረክትበት አቅጣጫ የሚቀመጥበት ይሆናል ብሏል።

ለበዓሉ አከባበር ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከኦሮሚያ ክልልና ፓስቶራሊስት ፎረም ኢትዮጵያ የተወከሉ አመራሮችና ባለሙያዎች ያሉባቸው ንዑሳን ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል።

በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት ጥር 17 ቀን 2014 በሚከበረው የአርብቶ አደሮች ቀን ከሁሉም አርብቶ አደር ክልሎችና አካባቢዎች ተወካይ አርብቶ አደሮች፣ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ የአርብቶ አደሩ አጋሮች፣ የዩኒቨርሲቲ ተወካዮች፣ ባለሃብቶችና ታዋቂ ግለሰቦች እንደሚታደሙ ተጠቁሟል።