በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት ተመለከቱ

178

ጥር 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን ወሎ ዩኒቨርሲቲንና ደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ተመለከቱ።

በቡድኑ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ወሎ ዩኒቨርሲቲን በመጠገን በሚቀጥለው ወር የመማር ማስተማር ሥራውን በከፊል እንደሚጀምር ተገልጿል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አሸባሪው ህወሓት በዩኒቨርሲቲውና በሆስፒታሉ ያደረሰውን ጉዳት በአምባሳደሩ ለተመራው ልኡካን ቡድን ገለጻ አድርገዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ወረራ በፈፀመበት ወቅት የዩኒቨርሲቲውን የተለያዩ ንብረቶች ዘርፎ መውሰዱንና ያልቻለውንም ማውደሙን ለልኡኩ አስረድተዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በተቋሙ ላይ የፈፀመው ጉዳትና ዝርፊያም ፈጥኖ ሥራ ለማስጀመር በማያስችል መልኩ መሆኑን ተናግረዋል።

አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ዩኒቨርሲቲው መልሶ እንዲቋቋም ድጋፍ እንደሚደረግ ባደረጉት ውይይት ወቅት መግለጻቸውን ዶክተር መንገሻ አስታውቀዋል።

በተጨማሪ በፈረንሳይ ካሉ አቻ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በማስተሳሰር የቴክኖሎጂና አሰራር ልምድ ልውውጥ እንዲደረግ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን ጠቅሰዋል።

ዶክተር መንገሻ እንዳሉት፤ በአምባሳደሩ የተመራ ልኡክ የተቋሙን ጉዳት ተዘዋውሮ መመልክቱ የሽብር ቡድኑ ያደረሰውን ጥፋት ለዓለም ህዝብ ለማሳወቅ ፋይዳው የጎላ ነው።

አንዳንድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን የሽብር ቡድኑን በመደገፍ የሚያሰራጩትን የውሸት ዘገባ ለማጋለጥ የጎላ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ ተቋማትንና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ተቋሙን መልሶ ለማደራጀትና የመማር ማስተማር ስራውን ለማስጀመር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ዶክተር መንገሻ ተናግረዋል።

“የሽብር ቡድኑ በዘመናዊ መንገድ የተደራጀውን ቤተሙከራ፣ ቤተ መጻህፍት፣ አይ.ሲ.ቲ፣ የመምህራንና የተማሪዎች መኖሪያ፣ የመማሪያና መመገቢያ ህንፃዎች ላይ ጉዳት ቢያደርስም ተጠግነው ለሥራ ዝግጁ እየሆኑ ይገኛሉ” ብለዋል።

የኤሌክትሪክና የውሃ መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ ሌሎች ለመማር ማስተማር ሥራው የሚያስፈልጉ ግብአቶች እየተሟሉ መሆኑንም አመልክተዋል።

“በየካቲት ወር መጀመሪያ የሕክምና ተማሪዎችን ተቀብለን ትምህርት ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት እያደረግን ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በወሩ መጨረሻ ደግሞ ሌሎች ነባር ተማሪዎችን እንደሚቀበሉ አስታውቀዋል።

የአስተዳደር ሰራተኞችና መምህራንም ለዚሁ ዝግጁ ናቸው ነው ያሉት።

የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሃይማኖት አየለ በበኩላቸው፤ ሆስፒታሉ ለምስራቅ አማራ፣ አፋርና ከፊል ትግራይ ህዝብ ተደራሽ ሆኖ ሲያገለግል የነበረ ቢሆንም በሽብር ቡድኑ ሙሉ በሙሉ መውደሙን ገልጸዋል።

“የሽብር ቡድኑ የጤና ተቋማትን ጨምሮ ሰብዓዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን መዝረፉ እና ማውደሙ ለህዝብ ያለውን የከፋ ጥላቻ በግልጽ ያሳያል” ብለዋል።

ዶክተር ሃይማኖት እንዳስታወቁት፤ ሆስፒታሉ በቅንጅት በተከናወነው ሥራ በአሁኑ ወቅት በከፊል ተስተካክሎ ስራ እንዲጀምር ተደርጓል።

የፈረንሳይ አምባሳደር ለሆስፒታሉ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን የገለጹት ዶክተር ሃይማኖት፤ “በአምባሳደሩ የተመራ ልዑክ ሆስፒታሉን መጎብኘቱ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር የሚያግዝ ነው” ብለዋል፡፡

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሃ ግብሮች የሚያስተምራቸው ከ26 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንደነበሩት ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼