በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና የማግኘት እንቅስቃሴ ወረታ የመጠየቅ ሳይሆን መብታችንን የማስከበር ጉዳይ ነው-ዩዌሪ ሙሴቬኒ

121

ጥር 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) “የአፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና እንዲኖራት የማድረግእንቅስቃሴ ወረታ ሳይሆን መብታችንን የማስከበር ጉዳይ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል” ሲሉ የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ገለጹ።

አፍሪካን በመወከል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ማሻሻያዎችን አስመልክቶ ድርድር እያደረጉ የሚገኙ የ10 የአፍሪካ አገራት ኮሚቴ(C-10) ተወካዮች የደረሱበትን ሂደት አስመልክቶ ትናንት በኡጋንዳ ካምፓላ ውይይት አድርገዋል።

የ10 የአፍሪካ አገራት ኮሚቴ ኬንያ፣ ኢኮቶሪያል ጊኒ፣ ናምቢያ፣ ዛምቢያ፣ ሊቢያ፣ አልጄሪያ፣ ሴራሊዮን፣ ሴኔጋል፣ ኡጋንዳና ኮንጎ ሪፐብሊክን የያዘ ነው።

ኮሚቴው አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ሁለት ቋሚ መቀመጫና በምክር ቤቱ ቋሚ ባልሆኑ ውክልናዎች ሁለት ተጨማሪ የአፍሪካ አገራትን መጨመር አላማው አድርጎ እየሰራ ይገኛል።

የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሁን ያለበት ቁመና ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት በኋላ የነበረውን ጊዜ እንጂ የዓለምን አሁናዊ ሁኔታ የሚወክል አይደለም ማለታቸውን የቻይናው የዜና ወኪል ዥንዋ ዘግቧል።

አፍሪካ ጥቅሞቿንና ፍላጎቷን ለማስጠበቅ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንደሚያስፈልጋትና ቋሚ ውክልና ማግኘቷ ምክር ቤቱ አሉታዊ ጉዳት በአህጉሪቷ ላይ እንዳያደርስ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ሕዝብ ያላት አፍሪካ በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ ማግኘት ይገባታል ብለዋል።

ዓለም አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና የማግኘት ጥያቄዋን መብትን የማስከበር ጉዳይ እንጂ ወረታ እንደመጠየቅ አድርጎ ሊያየው እንደማይገባም ነው ሙሴቬኒ የገለጹት።

የሴራሊዮን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ጆን ፍራንሲስ በበኩላቸው “በተመድ የጸጥታ ምክር ቤት 70 በመቶ ውይይት የሚያደረግባቸው ጉዳዮች አፍሪካ ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ ናቸው፤አፍሪካ በምክር ቤቱ እስካሁን ቋሚ መቀመጫ የላትም ይሄ በፍጹም ሊቀጥል አይገባውም” ብለዋል።

ጥያቄያችን ፍትሐዊ ውክልና የማግኘት ነው ያሉት ሚኒስትሩ አፍሪካውያን ችግሮች ሳይበግሯቸው በጋራ በጽናት በመቆም ትግሉን ከዳር ማድረስ እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች ኮሚሽነር ባንኮሌ አዶዬ የካምፓላው ውይይት አፍሪካ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት ያስፈልገዋል በሚል እያደረገች ያለውን ግፊትና ጥረት በአዲስ መልክ ዳግም ለመጀመር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሕብረት በእውተኛ ትብብርና በባለብዙ መድረኮች የዲፕሎማሲ ግንኙነት መርህ እንደሚያምን ተናግረዋል።

አፍሪካ የረጅም ጊዜ ሂደት ሊጠይቅ በሚችለው የተመድ ተቋማዊ የማሻሻያ ሂደት እጇን ሳትሰጥ የጀመረችውን ጉዞ መቀጠል አለባት ብለዋል።

የ10ሩ የአፍሪካ አገራት ኮሚቴ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ አስመልክቶ የሚደረጉ ውይይቶች ረጅም ጊዜ የፈጁና አንዳንድ ያደጉ አገራት ምክር ቤቱ አሁን ባለበት ቁመና የማስቀጠል ቁርጠኛ አቋም እንዳላቸው የታየበት እንደሆነ በመረጃው ተጠቅሷል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም