ዲያስፖራው በ ”በቃ” ንቅናቄና በዲጂታል ዲፕሎማሲ ለውጥ አምጥቷል–ሚኒስቴሩ

232

ጎንደር (ኢዜአ) ጥር 13/2014— ዲያስፖራው በ ”በቃ” ንቅናቄና በዲጅታል ዲፕሎማሲው የአገሩን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሰራው ሥራ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ።

ዲያስፖራው በዲፕሎማሲ የሚኖረውን አስተዋፅኦ በቀጣይ ለማሳደግ የሚያስችል አገር አቀፍ አውደ ጥናት በጎንደር ዩኒቨርሲቲና በከተማ አስተዳደሩ አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በመድረኩ ላይ እንዳሉት የአፍሪካ ህብረት ጉባኤን በኢትዮጵያ ለማካሄድ ውሳኔ ላይ ካደረሰው ምክንያት አንዱ የዲያስፖራው ወደ አገር ቤት በብዛት መምጣት ነው።

በተለያዩ አህጉራት የሚገኙ ዲያስፖራዎች በኢትዮጵያ ላይ የተነሱ አሉታዊ አስተሳሰቦችንና ዘገባዎችን በበቃ “ኖ ሞር” ንቅናቄና እና በዲጅታል ዲፕሎማሲ በመሞገት ለውጥ እንዲመጣ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

ዳያስፖራው ማህበረሰብ ባለፉት ሦስት ዓመታትም ከ9 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወደ ሃገር ውስጥ በመላክ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግርን ለመቀነስ የድርሻውን መወጣቱን ነው የገለጹት።

የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው በመምጣት አገር ከገጠማት ችግር እንድትወጣ የድርሻቸውን ለመውጣት ላሳዩት ቁርጠኝነት ሚኒስትር ዴኤታዋ ምስጋና አቅርበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት “እንደ ህንድ ያሉ አገራት ዲያስፖራውን ያሳተፈ ሥራ በመስራት ለእድገታቸው ተጠቅመውበታል” ብለዋል።

“ኢትዮጵያም በርካታ ዳያስፖራ ያላት አገር ብትሆንም በተለያዩ ገፊ ምንያቶች በአግባቡ መጠቀም አልቻለችም” ሲሉ ተናግረዋል።

አገራዊ ለውጡ ከመጣ ወዲህ ዲያስፖራውን በሁለንተናዊ አገራዊ ጉዳዮች ለማሳተፍ የተደረገው ጥረት በአሁኑ ወቅት ለውጥ እያመጣ በመሆኑ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን በበኩላቸው በውጭ የተማሩና የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዲያስፓራዎች በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በፈጠራና መሰል ጉዳዮች ለዩኒቨርሲቲው ያደረጉት ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

ምሁራን ወደ ሀገር መጥተው በማስተማር፣ ለምርምር የሚሆን ገንዘብ አፈላልገው በመላክና በማስተማሪያ ግብአት አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

”በቀጣይም  አስተዋጿቸውን በማስቀጠልና በጋራ በመደጋገፍ የአገርን ህልውና ማረጋገጥ ይኖርብናል” ሲሉ ገልጸዋል።

ዶክተር አስራት እንዳሉት ዲያስፖራው የሚሳተፍባቸውን የኢንቨስትመንት አማራጮች በመለየትና በማማከር አገልግሎት ለመስጠት ዩኒቨርሲቲው ሙሉ ዝግጅት አድርጓል።

“ጎንደር በመተማ ከሱዳን፣ በወልቃይት ከኤርትራ ጋር የምትገናኝ በመሆኑ የልማት ኮሪደር እንድትሆን አድርጓታል” ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ ናቸው።

ዲያስፖራዎች ወደ ጎንደር ከተማ መጥተው ማልማት ቢፈልጉ የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እንደማይለያቸው አረጋግጠዋል።

“ለከተማዋ ልማት እንቅፋት የሆኑ አሰራሮችን በመለየት መፍታት የሚያስችል የሶስት ዓመት መሪ ዕቅድ በማውጣት እየሰራን ነው” ሲሉም ገልፀዋል።

በመድረኩ ላይ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የዳያስፖራው ሚና፣ በጎንደር ከተማ የኢንቨስትመንት አመራጮችና ቀጣይ እይታዎች በሚሉና መሰል ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በምሁራን ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ይካሄድባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በአውደ ጥናቱ ላይ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሚቶ፣ ዲያስፖራዎች እንዲሁም ሌሎች ከፌደራልና ከክልሉ እንዲሁም ከዞንና ከከተማ አስተዳደር የመጡ አመራሮችና ምሁራን እየተሳተፉ ይገኛል።