በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ውሃ እና ጉልበት ቆጣቢውን የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂ ለማስፋት እየተሰራ ነው

286

አዲስ አበባ ጥር 13/2014(ኢዜአ) በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ውሃ፣ ጉልበትና ጊዜ ቆጣቢ የሆነውን የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ጋሻው ማሞ እንደገለጹት በወረዳው በበጋ ወራት በ13 ቀበሌዎች 867 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡

በአካባቢው በመስኖ የመጠቀም ፍላጎት ቢኖርም ከፍተኛ የውሃ እጥረት አለ ያሉት አቶ ጋሻው ችግሩን ለማቃለል አርሶ አደሩ ባለው የውሃ ሃብት የመስኖ ልማቱን እንዲከውን የጠብታ መስኖን በማስተዋወቅ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በሙከራ ደረጃም በወረዳው 60 አርሶ አደሮች ይህንኑ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለውን የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂ እንዲተገብሩ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም በ13ቱም ቀበሌዎች የጠብታ መስኖ ለማስጀመርና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ በሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የጠብታ መስኖው አርሶ አደሮች በትንሽ መሬት ከፍተኛ ምርት እንዲያመርቱ የሚያስችል መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

ቴክኖሎጂው ውሃ፣ ጉልበት እና ጊዜ ቆጣቢ እንዲሁም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ በወረዳው ለማስፋፋት በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

የኢራንቡቲ ቀበሌ ግብርና ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ አሸናፊ እሸቴ በበኩላቸው የቀበሌው አርሶ አደሮች በቴክኖሎጂው የመጠቀም ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ቴክኖሎጂው 90 በመቶ ውሃ የመቆጠብ አቅም ስላለውም በአርሶ አደሮች ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታ ተቀባይነትን አግኝቷል ብለዋል።

በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ 27 የገጠር ቀበሌዎች 48 ሺህ 680 ሄክታር መሬት በመኸር የሚታረስ ሲሆን አካባቢውም ትርፍ አምራች ከሚባሉት መካከል መሆኑን የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡