ኑሯቸውን በፊንላንድ ያደረጉ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

79

ባህር ዳር ጥር 12/2014 (ኢዜአ)…በፊንላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአሸባሪው ህወሓት ለተፈናቀሉ ወገኖች ማቋቋሚያ የሚሆን ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ።

በፊንላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑን በመወከል ድጋፉን ያስረከቡት ዶክተር ትግስት ቸርነት እንደገለጹት ገንዘቡ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸውን ወገኖች መልሶ ለማቋቋም የሚውል ነው።

በቀጣይም በክልሉ በአሸባሪ ቡድኑ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለማቋቋም፣ የወደሙ ተቋማትንና የመሰረተ ልማት አውታሮችን መልሶ ለመገንባት እየተደረገ ላለው ጥረት ስኬት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል።

አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የፈፀመውን ግፍና በደል እኛ ኢትዮጵያዊያን በተባበረ ክንድ ኢትዮጵያን መልሶ በመገንባት የእኩይ ድርጊቱን እርባናቢስነት በተግባር ለማሳየት የሚጠበቅብንን ሁሉ እንወጣለን ሲሉ ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያን የማፍረስ ዕቅዱን ለማሳካት ዓለም አቀፉን ማህብረሰብ ለማሳሳት የተጓዘበትን የሴራ ፖለቲካ በ''ኖ ሞር'' ዘመቻ በውጭ የምንኖር ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር በመሆን ሴራው እንዲከሽፍ አድርገናል ብለዋል።

በውጭ የምንኖር ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅ የጀመርነውን የዜግነት ዲፕሎማሲ ከመቸውም ጊዜ በላይ አጠናክረን ለመቀጠል ዝግጁ ነን ሲሉም አረጋግጠዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ በበኩላቸው በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በውጭ የሚኖሩ ኢዮጵያዊያንና ትውልደ ኢዮጵያዊያን ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

አሸባሪው የህወሐት ኢትዮጵያን በገዛበት 27 ዓመታት ኢትዮጵያን ለማፍረ አልሞ በሰራው የፖለቲካ ሴራ ሊነጣጥለን ረጅም ርቀት ቢጓዝም የከፈተብን ጦርነት አንድ እንድንሆን አድርጎናል ብለዋል።

አፈ ጉባኤዋ እንዳሉት የሽብር ቡድኑን የተሳሳተ ፕሮፓጋንዳ ለማክሸፍም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ያደረጉት የዜጋ ዲፕሎማሲ ተጋድሎ ኢትዮጵያን ከመፍረስ ታድጓታል።

በፊንላድ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አሁን ያሳዩትን ትብብራቸውንና ህብረታቸውን በቀጣይም ክልሉን መልሶ በመገንባት በሚደረገው ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ እታገኘሁ አደመ በበኩላቸው በአሸባሪ ህወሓት የደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የክልሉ መንግሥት እያደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ጥረት የዜጎችን ያልተቋረጠ ድጋፍ የሚጠይቅ በመሆኑ በቀጣይም ድጋፋቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ያደረጉት ድጋፍ በሽብር ቡድኑ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ለሚደረገው ተግባር በትክክል እንደሚውልም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም