በመዲናዋ አትላስ አካባቢ የተከሰተው የእሳት አደጋ በቁጥጥር ስር ዋለ

194

ጥር 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ አትላስ አካባቢ የተከሰተው የእሳት አደጋ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰለሞን ፍስሃ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የተከሰተውን የእሳት አደጋ ለማጥፋት 20 የእሳት ማጥፊያ ተሽከርካሪዎች ስራ ላይ ውለዋል።

የእሳት አደጋው የተከሰተበት አካባቢ ከኡራኤል ቤተክርስያን ጀርባ በተለምዶ አትላስ አካባቢ በሚገኙ የንግድ መጋዘኖች ላይ ነው።

የእሳት ቃጠሎው በደረሰባቸው መጋዘኖች ውስጥ የተለያዩ የባኞ ቤት እቃዎች፣ ጣውላና ሌሎችም በቀላሉ የሚቀጣጠሉ እቃዎች ስለነበሩ እሳቱን ለመቆጣጠር ፈታኝ እንደነበር ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

አደጋውን ለመቆጣጠር የእሳት አደጋ ሰራተኞች ፈጥነው በስፍራው በመገኘት እሳቱ እንዳይዛመትና እንዲጠፋ ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል ብለዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ የፖሊስና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች እሳቱን በመቆጣጠር ሂደት የነበራቸውን ተሳትፎ አድንቀዋል።

በመሆኑም በአደጋ ጊዜ ሰራተኞችና ሌሎችም ትብብር የእሳት አደጋው በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቀዋል።

የእሳት አደጋው መነሻ ምክንያት እና የደረሰው የጉዳት መጠን በቀጣይ የሚጣራ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼