የጥምቀት በዓል የአንድነትና የፍቅር መገለጫ ሆኖ እንዲቀጥል ጥረት እናደርጋለን

83

ድሬዳዋ፣ ጥር 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የጥምቀት በዓል የአንድነትና የፍቅር መገለጫነቱ እንዲቀጥል ጥረት እንደሚያደርጉ የድሬዳዋ ከተማ የበዓሉ ታዳሚዎች ተናገሩ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የበዓሉ  ታዳሚዎች እንዳሉት፤  በዓሉ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቱን አስጠብቀው ለትውልድ ከማስተላለፍ ባሻገር ኢትዮጵያዊነት መገለጫና ማሳያ ሆኖ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ።

ከአሜሪካ አትላንታ ከተማ የመጡት አቶ ሽመልስ በቀለ ኢትዮጵያ ካሏት ድንቅ ኃይማኖታዊ በዓላት መካከል ጥምቀት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዓሉ የጋራ መገለጫችን ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

በዓላት የቱሪስት መዳረሻ ሆነው ለወጣቱ የሥራ ዕድልና ለሀገር  ዕድገት ድርሻ እንዲኖራቸው በስፋት መሰራት እንዳለበትም ተናግረዋል።

በዓሉ ከኢትዮጵያ አልፎ ቅርስነቱ  የዓለም ሆኗል ያሉት ወይዘሮ አበባ ግርማ፤ ይህ የሀገር ሃብት ለልማት እንዲውልና ለትውልድ እንዲተላለፍ ልጆቻቸውን በማስተማር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ጌትነት ግርማ በበኩላቸው፤ በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበውን የጥምቀት በዓል ለመጎብኘት የሚመጡ የውጭ ቱሪስቶችን  ቁጥር ለማብዛት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ይህንን የሀገር ሃብት ለኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት በተገቢው መንገድ እንዲውል የሚመለከታቸው አካላትና ዳያስፖራዎች ቢያግዙ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

ወጣት ኢዮብ ተሰማ፤ ወጣቶች ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በዓሉ ያለምንም ፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ በመሥራት ላይ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም